Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄደ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄደ ጀመረ።

ምክር ቤቱ 2ኛ የስራ ዘመን 44ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ ማካሄድ በጀመረበት ወቅት የከተማ አስተዳደሩን የአስፈፃሚ አካላት የ2012 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ ቡህ ቀርቧል።

ምክትል ከንቲባው በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት በበጀት ዓመቱ አንድ ቢሊየን 259 ሚሊየን 757 ሺህ 219 ብር መሰብሰቡንና ይህም የዕቅዱን 84 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2012 በጀት ዓመት 113 አዳዲስ የካፒታል በጀት ፕሮጀክቶች እና 65 ነባር በጠቅላላው 178 ፕሮጀክቶች ሲከናወኑ እንደነበር የገለፁት አቶ አህመድ፥ ከዚህ ውስጥ 57 መጠናቀቃቸውን፣ 81 በግንባታ ላይ መሆናቸውን እና 19 ፕሮጀክቶች ደግሞ መታጠፋቸውንና አራቱ አለመጀመራቸውን በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።

ለወጣቶች በተመደበ ተዘዋዋሪ ፈንድ አማካኝነት 878 አባላት ላሏቸው 165 ኢንተርፕራይዞች ከ28 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ በብድር መሰጠቱንና ለወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ 38 አነስተኛ እና 13 መካከለኛ ኢንደስትሪዎችን የማቋቋም እንዲሁም 144 ነባር ኢንደስትሪዎችን የማጠናከር ስራ እንዲሁም ስድስት አነስተኛ ኢንደስትሪዎችን ወደ መካከለኛ፣ ስምንቱን ደግሞ ወደ ከፍተኛ የማሸጋገርና የማብቃት ስራ መከናወኑን ነው ያመለከቱት።

እንደ ምክትል ከንቲባው ሪፖርት በዚሁ በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ለ320 ባለሃብቶች በማምረቻ፣ በግንባታ እና በአገልግሎት ዘርፎች ለመሰማራት ባቀረቡት ፕሮፖዛል መሰረት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በ2ኛ የስራ ዘመን 44ኛ መደበኛ ጉባኤው በምክትል ከንቲባው በቀረበው የ2012 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ላይ እየተወያየ ይገኛል።

ጉባኤው እስከ ነገ ሐምሌ 30 ቀን 2012 የሚቆይ ሲሆን፥ የአስተዳደሩ ፍርድ ቤቶች፣ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትና የመገናኛ ብዙሃን ድርጅት የ2012 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2013 መሪ እቅድ ላይ እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደርን የ2013 በጀትና መሪ እቅድ ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ ጉባኤውን ነገ ሲያጠናቅቅ የተለያዩ ሹመቶችን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.