Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ሆኖ የቀረበለትንየከተማ አስተዳደሩን የ2013 በጀትአጸደቀ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 30 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ሆኖ የቀረበለትን የከተማ አስተዳደሩን የ2013 በጀት አጽድቋል።
 
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 2ኛ የስራ ዘመን 44ኛ መደበኛ ጉባኤውን የአስተዳደሩን የ2013 በጀት ጨምሮ የተለያዩ ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቋል።
 
በዚህም ምክር ቤቱ ለ2013 በጀት ዓመት 4 ቢሊየን 214 ሚሊየን 594 ሺህ 256 ብር ያፀደቀ ሲሆን÷ ከበጀቱ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ከፌደራል መንግስት ድጎማ፣ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ከከተማ አስተዳደሩ ከሚሰበሰብ ግብርና 734 ሚሊየን ብር ከተለያዩ የልማት አጋሮች ከሚገኝ እንደሚሸፈን ተገልጿል።
 
ከፀደቀው በጀት ውስጥ 55 በመቶው ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል ሲሆን ÷ ቀሪው 45 በመቶ ለመደበኛ በጀት እንደሚሆንም ነው የተገለጸው።
 
የበጀቱ ምንጭም ከፌደራል መንግስት ከሚገኝ ድጎማና ከከተማ አስተዳደሩ ከሚሰበሰብ ግብር መሆኑም ተመላክቷል።
 
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት በሁለት ቀናት ቆይታው የ2012 በጀት ዓመት የአስተዳደሩ አስፈፃሚ አካላት፣የፍርድ ቤቶች፣የዋና ኦዲተርና የመገናኛ ብዙሃን ድርጅት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2013 መሪ እቅድ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ፀድቋል።
 
ጉባኤው በመጨረሻም ወይዘሮ ለምለም በዛብህን ለጤና ቢሮ እንዲሁም አቶ ገበየሁ ጥላሁንን ለመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ በኃላፊነት እንዲሁም ሦስት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ሹመትና አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛን ሹመት በማፅደቅ ተጠናቋል።
 
በተሾመ ኃይሉ
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.