Fana: At a Speed of Life!

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ለፋና ላምሮት አሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት አበረከተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአስረኛው ምዕራፍ የፋና ላምሮት የድምጻውያን ውድድር አንደኛ ለወጣችው ያለምወርቅ ጀንበሩ እና ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ውድድሩን ላጠናቀቀው ደሳለኝ አበበ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የገንዘብ ሽልማት አበረከተላቸው፡፡

በዚሁ መሰረት÷ አንደኛ ለወጣችው ያለምወርቅ ጀንበሩ የ100 ሺህ እና ሦስተኛ ደረጃ ለወጣው ደሳለኝ አበበ የ50 ሺህ ብር ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

በተመሳሳይ የጎንደር ዩንቨርሲቲ ለሁለቱም አሸናፊ ድምጻውያን ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቷል፡፡

የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ደግሞ የገንዘብና የህክምና ወጪ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኛው÷በፋና ላምሮት የድምጻውያን ውድድር አሸናፊ የሆናችሁ የጥበብ ሰዎች ጉዞአችሁ ረጅም ስለሆነ በትጋት ልትሰሩ ይገባል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የሚያደርጋቸውን ድጋፎችም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የጎንደር ባህል ማዕከል ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ዋሴ ነጋሽ በበኩላቸው÷ እናንተ ለሌሎች ጀማሪ የኪነ ጥበብ አፍቃሪያን ትልቅ መሰረት ጥላችኋል ነው ያሉት፡፡

የፋና ላምሮት አሸናፊ የዓለም ወርቅ ጀንበሩ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ደሳለኝ አበበ ዛሬ ጎንደር አጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ÷ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይን ጨምሮ የጥበብ ሰዎችና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በምናለ አየነው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.