Fana: At a Speed of Life!

ዶክተር ሊያ ታደሰ ማህበረሰቡ እየተሰጠ ያለውን የኮቪድ19 ክትባት እንዲወስድ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ማህበረሰቡ እየተሰጠ ያለውን የኮቪድ19 ክትባት እንዲወስድ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ሚኒስትሯ የኮቪድ19 ወረርሽኝ አሁንም ብዙዎችን እየጎዳ መሆኑን እና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ክትባቱን መውሰድ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል።

የተከተቡ ሰዎች ቫይረሱን ለመቋቋም የተሻለ አቅም አላቸው ያሉት ሚኒስትሯ በጽኑ ለመታመምም ሆነ በቫይረሱ ለመሞት ያላቸው እድል ዝቅተኛ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እስካሁን 24 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ክትባት የወሰዱ ቢሆንም 342 ሺህ 108 ሰዎች ብቻ ከስድስት ወር በኋላ የሚሰጠውን የማጠናከሪያ ክትባት መውሰዳቸውንም አንስተዋል።

በዚህም ተደራሽነትን ለማሻሻል ሌላ ዙር የኮቪድ19 የክትባት ዘመቻ መጀመሩን አመላክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ በኮቪድ19 ተይዘው የሆስፒታል ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ እያየን ነው ያሉት ሚኒስትሯ በቫይረሱ የሚያዙት በአብዛኛው ክትባት ያልወሰዱ ናቸው ብለዋል።

ስለዚህ እድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ክትባቱን እንዲወስዱ እና ክትባት ከወሰዱ 6 ወር ያለፋቸው የማጠናከሪያ ክትባት በመውሰድ ራሳቸውን እና ማህበረሰቡን እንዲከላከሉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሦስተኛው ዙር የኮቪድ19 ክትባት ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እየተሰጠ ይገኛል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.