Fana: At a Speed of Life!

ለሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት የሚሆን 1 ሺህ ሄክታር መሬት ምንጣሮ በቀጣይ ሳምንት ይጀመራል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት የሚሆን 1 ሺህ ሄክታር የመሬት ምንጣሮ ስራ በመጪው ሳምንት እንደሚጀመር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ።

ለምንጣሮ ስራው 300 ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት መደራጀታቸውም ታውቋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንደገለጹት ቀደም ሲል በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ተጀምሮ የነበረው የደን ምንጣሮ ውጤታማ አልነበረም።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ስለ መሆኑ ገልጸው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ግድቡን በመጪው ሐምሌ ውሃ ለመሙላት በታቀደው መሰረት ክልሉ ለዚህ የሚሆነውን መሬት የደን ምንጣሮ ለማካሄድ መዘጋጀቱን አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በጥቃቅንና አነስተኛ ከተደራጁ ወጣቶች በተጨማሪ በቀን ስራ የሚተዳደሩ ዜጎችም በምንጣሮ ስራው ይሳተፋሉ።

1 ሺህ ሄክታር መሬት ለመመንጠርና ለተያያዥ ስራዎች ከ25 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀከት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው፥ የግድቡን ግንባታ በዕቅዱ መሰረት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ውሃ ለመያዝ በተዘጋጀው ግድብ ውስጥ የሚተከሉ የብረታብረት ስራዎች ተጠናቀው ኮንክሪት እየተሞላባቸውና የውሃ መግቢያ መቆጣጠሪያ በሮችም እየተገጠሙ መሆኑን ገልጸዋል።

አብዛኛው ስራ መጠናቀቁን የገለጹት ኢንጂነሩ ቀሪ ስራዎችም በተያዘላቸው ጊዜ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።

በሌላ በኩል የፕሮጀክቱ የግንባታ ሠራተኞች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ጠብቀው ስራቸውን እንዲያከናውኑ እየተወሰዱ ስለሚገኙ እርምጃዎች ኢንጅነር ክፍሌ አስረድተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 73 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል።

በመጪው ሐምሌ በግድቡ የሚሞላው የውሃ መጠን 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ኪዩቢክ ሊትር ሲሆን፥ ይህም የግድቡን ሁለት ተርባይኖች የሚያንቀሳቅስ ነው።

በሚቀጥለው ዓመት በተመሳሳይ 13 ነጥብ 5 ቢሊየን ኪዩቢክ ሊትር ውሃ ይሞላል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.