Fana: At a Speed of Life!

በሃገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባለሃብቶች ሽርክና 560 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ 560 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በሃገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባለሃብቶች ሽርክና እየተተገበሩ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር መኮንን ኃይሉ እንደተናገሩት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ትግበራው የሀገሪቷን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ከማረጋገጥ ባለፈ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ያግዛል።

ከዚህ ባለፈም በዓለም አቀፍ ገበያ የተወዳዳሪነት ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ከሽርክና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ መካከል 182ቱ ምርትና አገልግሎት መስጠትመጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

ሌሎች 114 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ደግሞ በትግበራ ሂደት ላይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 264 በቅድመ ትግበራ ሂደት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ቻይናውያን ባለሃብቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር በሽርክና በመስራት ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ የአሜሪካ፣ የሕንድ፣ የጃፓን፣ የካናዳ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የሱዳንና የስፔን ባለሃብቶችም እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።

ባለሃብቶቹ ከሚሳተፉባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች የማምረቻ ኢንዱስትሪ 350 ፕሮጀክቶችን በመያዝ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።

ግብርና፣ ቤቶች ግንባታና ማሽነሪ፣ የግንባታው ዘርፍ፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ የማስጎብኘት አገልግሎትና ትራንስፖርት፣ ጤና፣ ትምህርትና ሌሎችም በሽርክና የሚሰሩባቸው ዘርፎች እንደሆኑ መናገራቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.