Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል አደጋን ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ከ220 ሚሊየን ብር በላይ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 12 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ከ220 ሚሊየን ብር በላይ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ከነገ ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገባው ይህ ፕሮጀክት በክልሉ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የማይበገር ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ሥራ የሚያግዝ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን ለማዘመን የሚያስችልና የባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በክልሉ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ቀድሞ መለየትና አደጋ ከተከሰተ በኋላ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ እና መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አብርሃም አበበ በበኩላቸው÷ የአውሮፖ ኅብረት በኢትዮጵያ አራት ክልሎች (በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሶማሌ) የአደጋ ስጋትን ለመከላከልና ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ይህ የአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክት አደጋ ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የሚያስችል እና በአራቱ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ ያልተማከለ የአደጋ ሥራ አመራር አደረጃጀትን በማዋቀር የሥራውን ተፈፃሚነት እንደሚከታተል መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.