Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ህብረት በሀሰተኛ ሰነድ ከባንክ ሂሳቡ ገንዘብ ለማውጣት የተደረገውን ሙከራ አወገዘ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት በፈረንጆቹ ሚያዝያ 15 ቀን 2024 በዋና መስሪያ ቤቱ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ለማዛወር የተደረገውን ሙከራ አውግዟል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች እና የህብረቱ የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ምንም ገንዘብ እንዳይወጣ በማድረግ የተቃጣውን የማጭበርበር ሙከራ ለማክሸፍ ለወሰዱት ፈጣን እርምጃም አድናቆቱን ገልጿል።

በወቅቱ የተፈጠረው ክስተትም የአፍሪካ ህብረት ተቀጣሪ ባልሆነ ግለሰብ በአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሀሰተኛ የክፍያ ማዘዋወሪያ ትዕዛዝ መቅረቡን አመላክቷል።

ህብረቱ እንደገለፀው፤ የክፍያ ማዘዋወሪያ ትዕዛዞቹም በግንባታ እና የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች ስር ለተለያዩ አካላት የሚከፈል ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆነ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ነበር፡፡

ይሁንና የህብረቱ የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት በሰነዶቹ ላይ ባደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ ሰነዶቹ ሀሰተኛ ሆነው በመገኘታቸው ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳይወጣ በመደረጉ ህብረቱን ከኪሳራ መታደግ እንደተቻለ አመላክቷል፡፡

መረጃ የደረሳቸው የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃላፊዎችም ግለሰቡንና በማጭበርበር ተግባሩ የተሳታፉ ተባባሪዎቹን አስፈላጊውን የምርመራ ሂደት ለማከናወን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ነው የጠቀሰው፡፡

የተቃጣውን የማጭበርበር ሙከራ በፅኑ ያወገዘው የአፍሪካ ህብረት፤ ጉዳዩን በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለው መሆኑንም ነው በመግለጫው ያመላከተው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ በመድረስ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረጋቸውም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምስጋና አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.