Fana: At a Speed of Life!

በአውሮፓ የድርቅ አደጋ ወንዞችን እያደረቀ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ የተከሰተው ድርቅ ወንዞችን እያደረቀ፣ ዓሳዎችን እየገደለ እና የእህልን ሰብልንም እያደረቀ ነው ሲል አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

እንደ ዘገባው፥ በአንድ ወቅት ወንዝ የሚገማሸርበት ሥፍራ አሁን ላይ አቧራ እና በሺዎች የሚቆጠሩ የሞቱ ዓሳዎች የሚታዩበት ሆኗል፡፡

በፈረንሳይ በርገንዲ ክልል በሉክስ መንደር ውስጥ የሚገኘው ቲል የተባለው ወንዝ በረድፍ በተተከሉና በተዋቡ ዛፎች መካከል የሚገኘውን  ሰፊ ጉድጓድ ይሸፍን እንደነበረ እና አሁን ላይ ግን መድረቁን ነው ዘገባው ያመለከተው።

በስፔን ከሚገኙ ደረቅና የተሰነጣጠቁ የውኃ ማጠራቀሚያዎች በፈረንሳይ  ባሉ ዋና ዋና መስመሮች የሚወርደው የውሃ መጠን እየቀነሰ መምጣት ድርቅ በአውሮፓ አህጉር ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ግማሽ ያህሉን የውሃ አካል እያጠቃ እንደሚገኝ ያሳያል፡፡

በምዕራብ፣ መካከለኛው እና ደቡባዊ አውሮፓ ለሁለት ወራት ይህ ነው የሚባል  ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ የተከሰተው ድርቅ በ500 ዓመታት ውስጥ ታይቶ እንደማይታወቅ ባለሙያዎች መናገራቸውን ዘገባው አያይዞ ጠቅሷል፡፡

ይህ  ከፍተኛ ሙቀት እና የከፋ ድርቅ በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ አዲስ የእሳት ቃጠሎ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል፡፡

በአገሪቱ በአንድ ሌሊት ተቀስቅሶ ለቀናት ሲቀጣጠል የቆየ የሰደድ እሳት  ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም ተዘግቧል።

ከጀርመን፣ ሮማኒያ እና ግሪክ የመጡ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ፈረንሳይ በጂሮንዴ የቦርዶ የወይን ማሳ አካባቢ እንዲሁም ከመላው አውሮፓ የመጡ ሌሎችም በሰሜን ምዕራብ ብሪትኒ ውስጥ ያለውን እሳት ጨምሮ በሌሎች ግንባሮች ለመዋጋት በአካባቢው  እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

ይህ ደረቅ የአየር ሁኔታ በዚሁ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቃል ሲሉ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

በመሆኑም የሚስተዋለውን የአየር ሁኔታ ከግምት በማስገባት አዲስ ሊከሰት የሚችለው የእሳት አደጋ መዘዙ እጅግ የከፋ ይሆናል ሲል የጂሮንዴ ግዛት ማስጠንቀቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታዎችን እያባባሰ እንደሆነ፣ ሞቃታማው አየር ፀባይ ትነት ሲያጣድፈው፣ የተጠሙ እፅዋት ብዙ እርጥበት ስለሚወስዱ እና በክረምት ወራት የበረዶ ዝናብ ስለሚቀንስ በበጋ ለመስኖ የሚውለውን የንፁህ ውሃ አቅርቦት ይገድባል በማለትም ባለሙያዎቹ ተንትነዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአየር ንብርት ቀውሱ አውሮፓን ብቻ ሳይሆን ምሥራቅ አፍሪካን፣ ምዕራብ አሜሪካ እና ሰሜናዊ ሜክሲኮንም እንደሚያጠቃ ተመላክቷል፡፡

 

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.