Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርት የፊታችን ሰኞ ይጀመራል

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርት የፊታችን ሰኞ እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጭ ላሉ ተማሪዎች ደግሞ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት ለመጀመር መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ተጨማሪ 2 ሺህ 300 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ያነሱት የቢሮ ሃላፊው በአንድ ክፍል 25 ተማሪዎች በአንድ ወንበር ደግሞ አንድ ተማሪ ተቀምጦ እንደሚማርም ገልጸዋል፡፡

ማንም ተማሪ በክፍል ውስጥም ሆነ ከክፍል ውጭ ከአፍና አፍንጫ ጭምብል ውጭ መንቀሳቀስ አይችልምም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጭ ያሉ ተማሪዎች የአንድ ወር ክለሳ ይሰጣቸዋል ነው የተባለው።

ለ8ኛ እና ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ የ45 ቀናት የክለሳ ትምህርት በመስጠት ለፈተና ዝግጁ እንዲሆኑ እንደሚደረግም በመግለጫው ተነስቷል፡፡

ትምህርቱ በፈረቃ የሚሰጥ ሲሆን አንደኛው ፈረቃ ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ ሁለተኛው ፈረቃ ደግሞ ማክሰኞ፣ሐሙስ እና ቅዳሜ ይሆናል፡፡

የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩም በከፍተኛ ጥንቃቄ ይቀጥላል ነው የተባለው።

አሁን ላይም በየትምህርት ቤቶቹ አስፈላጊው የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶችን የማሰባሰብ እና የማሰራጨት ስራዎች እየተሰሩ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ በሚገኙ 513 ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት ክሊኒክ ይቋቋማል ተብሏል።

ይህም ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው በስነ ልቦና እና አካላዊ ጤናቸው እንዲጠበቅ እንደሚያደርግ ታምኖበታል።

በአንድ ትምህርት ቤት አራት የጤና ባለሙያ የሚመደብ ሲሆን ለዚህም የ2 ሺህ 52 የጤና ባለሙያዎች ቅጥር እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

በምስክር ስናፍቅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.