Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ለሁለት አዳዲስ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች ፈቃድ የመስጠት ሂደት እስከ መጋቢት ወር ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ለሁለት አዳዲስ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች ፈቃድ የመስጠት ሂደት እስከ መጋቢት ወር ይጠናቀቃል ተብሏል።
የቴሌኮሙዩኒኬሽን ማሻሻያ ስራዎች አካል በሆነው ለአዲስ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ መስጠት ሂደት ላይ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ እንደገለጹት ለሁለት ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት የጨረታ ሰነድ በመጠናቀቅ ላይ ነው።
ጨረታው በሚቀጥለው ወር እንደሚወጣ የተገለፀ ሲሆን ጨረታው ከ40 እስከ 50 ቀኖች ክፍት ይሆናል ነው የተባለው።
እየተከናወኑ በሚገኙ እያንዳንዱ ስራዎች ለተሻለ አገልግሎት፣ ለደንበኞች መብት እና ለብሔራዊ ደህንነት ልዩ ጥንቃቄ እንደተሠጠም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
የአዳዲስ ኦፕሬተሮች መግባት ለሀገር ውስጥ የቴሌኮሙዩኒኬሽን እና አይ ሲ ቲ ኩባንያዎች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ተገልጿል ።
ስራውን በተሳካ መንገድ ለማስኬድም በኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን 16 መመሪያዎች እንደተዘጋጁም ነው በውይይት መድረኩ ላይ የተነገረው ።
የቴሌኮሙዩኒኬሽን ፈቃድ መመሪያ፣ የተገልጋዮች መብት እና ጥበቃ መመሪያ፣ የክርክር መፍቻ መመሪያ፣ የአገልግሎት ጥራት መመሪያ፣ መሰረተ ልማት መጋራት እና ኮሌክሽን መመሪያ፣ የሁሉን አቀፍ ተደራሽነት እና አገልግሎት መመሪያ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁጥር መመሪያ፣ ኢንተር ኮኔክሽን መመሪያ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ታሪፍ መመሪያ፣ መሬትና ህንጻን ለቴሌኮሙዩኑኬሽን መስመሮች ስለመጠቀም መመሪያ፣ የሁሉን ዓቀፍ ተደራሽነትና አገልግሎት ፈንድ መመሪያ፣ የኢንተርኔት ፕሮቶኮል አድራሻ እና የዶሜይን ስም መመሪያ፣ የውድድር መመሪያ እና የሲም ካርድ ምዝገባ መመሪያዎች መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል።
ለአዳዲሶቹ አፕሬተሮች ሚሰጠው ፈቃድ የሞባይል፣ የኢንተርኔት እና የፊክስድ ኔትዎርክ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ በተቀናጀ መልኩ መስጠት የሚያስችል መሆኑም ነው የተገለጸው።
በዓላዛር ታደለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.