Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት ፥ በክልሉ በ2003 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም በሙከራ ደረጃ በሶስት ወረዳዎች ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በዘርፉ የህብረተሰቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጨመረ ነው።

እንደ ዶክተር ዲላሞ ገለጻ ፥ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራም አስቀድሞ በሚከፈል አነስተኛ መዋጮ አማካኝነት ለህክምና የሚወጣውን ያልተጠበቀ ወጪን በመቀነስ የህብረተሰቡን ጤና ያረጋግጣል ።

ሆኖም በየጊዜው የአባልነት ምጣኔ ከፍ በማድረግ ህብረተሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም እንደ ክልል ከተያዘው ግብ አንጻር ሲመዘን የሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ለማለት አያስደፍርም ሲሉም ጠቁመዋል።

በክልሉ በ2013 በጀት ዓመት እንቅስቃሴ ከተጀመረባቸው 152 ወረዳዎች ውስጥ 136 ወረዳዎች ለአባላቶቻቸው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም አንስተዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ፥ በክልሉ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ እማወራዎች ወይም አባወራዎችን አባል በማድረግ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆነዋል።

እንዲሁም ከ238 ሚሊየን በላይ ብር መዋጮ በመሰብሰብ የጤና ተቋማትን የውስጥ ገቢ ማሳደግ እንደተቻለም ማስረዳታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.