Fana: At a Speed of Life!

ቱርክ ዓለም ላይ የረሃብ አደጋ ሥጋት ሳይባባስ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እልባት እንዲሰጠው ጠየቀች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት በዓለም ላይ የተከሰተውን የረሃብ አደጋ እንዳያባብስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትብብር እንዲሠራ ተመድ ባካሄደው የከፍተኛ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ቱርክ ጠየቀች፡፡

ተመድ “በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በድርጊት የማረጋገጥ ጥሪ ” በሚል መሪ ቃል የከፍተኛ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአሜሪካ አካሂዷል፡፡

በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ፥ ሀገራቱ ከጦርነቱ በፊት በምግብ አቅርቦት እና ምርት ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

በመካከላቸው ከተከሰተው ግጭት ወዲህ ግን በቂ ምርት ማምረት እንዳልቻሉ ናብሎም በወጪ ንግድ ሲሸፍኑት የነበረውን የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የምግብ አቅርቦት ፍላጎት መሸፈን እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየፈጸመች ያለችው ጥቃት ለሀገራቱ ብሎም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ ፈተና ሆኗልም ነው ያሉት።፡

በመሆኑም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመተባበር ሁለቱ ሀገራት ከግጭት ወጥተው ሥምምነት ላይ የሚደርሱበትን የሠላም አማራጭ መፈለግ እንዳለበትና ረሃብ እንዳይባባስ እንዲሠራ ጠይቀዋል።

አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ 800 ሚሊየን ህዝብ እንደተራበ የገለጹ ሲሆን ለረሃቡ ቀውስ ጦርነት እና ግጭቶች ዋነኛ አባባሽ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ደግሞ 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚገኘው በግጭት ቀጠናዎች አቅራቢያ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ቱርክ ከተባበሩት መንግስታት ጎን በመቆም ማናቸውንም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና ተልዕኮዎች ለመፈጸም ዝግጁ ናት ማለታቸውን የዘገበው አናዱሉ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.