Fana: At a Speed of Life!

ንግድ ቢሮ በዘይት ዋጋ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በዘይት ዋጋ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አከበረኝ ውጋገን በቅርቡ በዘይት  ዋጋ ላይ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ምክንያታዊ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህን ተከትሎም  ዋጋውን ለማረጋጋት  የንግድ ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ  ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱም የዘይት ዋጋ ከሁለት ወር በፊት ወደ ነበረበት የመሸጫ ዋጋ እንዲመለስ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ይሁን እንጂ በስምምነቱ መሰረት ዘይት ዋጋ ቅናሽ አለማሳየቱን በመዲናዋ ጉዳዩ ለመከታተል የተቋቋመው ግብረ ሃይል በዳረገው ቅኝት ማረጋገጡን አንስተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ቢሮው ባለ 5 ሊትሩን ዘይት ከ360 ብር በላይ በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡

በዚህ መሰረትም በትናንትናው ዕለት 240 በሚደርሱ የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገ አሰሳ 10 የሚሆኑት ከስምምነቱ ውጪ ሲሸጡ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አከበረኝ ውጋገን  ፣ ከዛሬ ጀምሮም  አምስት ሊትሩንን ዘይት 360  ብር በላይ  በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ የማሸግ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም ነጋዴዎች ምርታቸውን ወደ ክልሎች ለማውጣት ሙከራ ያደርጋሉ የሚሉት ምክትል ሃላፊው ይህንን ለመቆጣጠርም ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የዘይት አስመጪዎች እና አከፋፋዮች በተሰጣቸው የንግድ ፈቃድ ብቻ እንዲሰሩ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግም አውስተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም የአቅርቦት ፍላጎትን ማሳደግ ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን የገለጹት አቶ አከበረኝ ለዚህም፣ በዘርፉ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ ተቋማትን ምርት ለመጨመር ይሰራል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከውጪ የሚያስገቡ ነጋዴዎች ጉምሩክ አካባቢ የሚያጋጥማቸውን ችግር በመቅረፍ በፍጥነት ወደ ተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.