Fana: At a Speed of Life!

አገራዊ የምክክር ሂደቱ እንዲሳካ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስትን በመገንባት ሂደት ሚናው ከፍተኛ በሆነውና በቅርቡ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት ሲሉ ምሁራን ተናገሩ ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የታሪክ እና የህግ ምሁራን የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ ያሉ አጋጣሚዎችን በአግባቡ በመጠቀም በቀጣይ ሂደቶች ሁሉ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የህግ መምህር እንዲሁም ተመራማሪው ዶክተር አልማው ክፍሌ÷ አካታችነት፣ ጠንካራ ተቋማዊ አሰራርን እውን ማድረግ እና ለኮሚሽኑ የገቢ ምንጭን በግልጽ ማስቀመጥን የመሰሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ስለ ሂደቱ ለህዝብ መረጃ ለመስጠት የሚታስችል የኮሙኒኬሽን አሰራርና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መተግበር እንደሚገባም ዶክተር አልማው ክፍሌ አብራርተዋል ፡፡

የታሪክና ባህል ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር አህመድ ዘከሪያ እና በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ ሃይሉ ነጋ እንዳሉት÷ ዜጎች በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ ይቆሙ ዘንድ ከፍ ያለ ሚና እንዳለው ለሚታመንበት ኮሚሽንና እና የምክክር ሂደቱን የሚያስተናብሩ ባለድርሻዎችን ወደ ፊት ለማምጣት በሚከወኑ ስራዎች በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ለራስ በሚበጅ መልኩ መጠቀምንም ምሁራኑ እንደ ምክረ ሀሳብ አስቀምጠዋል፡፡

የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሰል አገራዊ ምክክሮችን ለማድረግ የሄዱባቸው ርቀቶች በውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ፍሬ እንዳያፈሩ መደረጋቸውን ያመለከቱት ምሁራኑ፥ መሰል ምክክሮች ከግብ እንዳይደርሱ የሚያደርጉ አሉታዊ ሚናዎችን ለማስቀረት መሰራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ሌሎች ዜጎችም በሀገራዊ ሃላፊነት መንፈስ ሊሰሩ እንደሚገባም ምሁራኑ ምክረ ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽንን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት በይቻላል መንፈስ መነሳት እና ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባም ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡

በአወል አበራ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.