Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እየተቀዳጀች ያለችው ድል የውስጥና የውጭ ጠላቶቿን የሃፍረት ካባ እንዳከናነበ የተለያዩ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እየተቀዳጀች ያለችው ድል የውስጥና የውጭ ጠላቶቿን የሃፍረት ካባ እንዳከናነበ የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮች ገለፁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮቹ በፋና ቴሌቪዥን “ስለ ኢትዮጵያ ” የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራም ላይ ቀርበው ውይይት አድርገዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወሉ አብዲ በተገኘው ድል በጣም ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው፥ ድሉ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ በብዙ መስዋትነት የተገኘ የመላ ኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካዊያን እና በአጠቃላይ የጥቁሮች ድልም ጭምር ነው ብለዋል፡፡

እንደ ኦሮሚያ ክልል ከሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ጦርነት ባልተናነሰ ሁኔታ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በወያኔ እና በተላላኪው ሸኔ አካባቢውን የሁከት ቀጠና ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎብናል ያሉት አቶ አወሉ፥ በደራ፣ ጎሀ ፂዮን እና በፍቼ መስመር በኩል፤ በምስራቁ አቅጣጫም በፈንታሌ፣ ቦሰት፣ ሚሌ መስመር፣ ሸዋ ሮቢት፤ በደቡብ መቂ አካባቢ፤ በደቡብ ምስራቅ ሽዋ አካባቢ እና በሌሎች አካባቢዎች ህወሃት እና ሸኔ ከፍተኛ የማወክ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በክልሉ ህዝብ እና በጸጥታ ሃይሉ ቅንጅታዊ ስራ ያሰቡት የማተራመስ ስራ ሊሳካላቸው እንዳለቻለ ተናግረዋል፡፡

ሸኔ እና ህወሃት ያልተቀደሰ ጋብቻ የፈጸሙት በቅርብ ጊዜ አይደለም ያሉት አቶ አወሉ፥ ከ1983 ጀምሮ የሽብር ስራቸውን በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል ነው ያሉት፡፡

ሸኔ ከኦሮሞ ህዝብ ባህልና እሴት ያፈነገጠ በፍጹም ተሰምተውም፤ ታይተውም የማይታወቁ ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ ያለና የክልሉን ሰላም ለመረበሽ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ሆኖም ህዝቡ እና የጸጥታ ሃይሉ በጋራ የአሸባሪውን አከርካሪ እየመቱ በመሆኑ በቅርቡ እንደሚያበቃለት አልጠራጠርም ብለዋል አቶ አወሉ፡፡

“ህዝባችን በአብዛኛው ከአሸባሪ ቡድኑ ነጻ ስለወጣ እና ጠላቶቻችን ቅስማቸው ስለተሰበረ ደስታ ተሰምቶኛል ደስታዬ ሙሉ የሚሆነው ግን አሸባሪው ቡድን ሙሉ በሙሉ ሲደመሰስ ነው” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር ናቸው።

በአማራ ክልል አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዘባቸው አካባቢዎች ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ህዝብ መፈናቀሉን ዶክተር ጌታቸው ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ የተፈናቀሉት ወደ ቀያቸው እና ህዝቡ ወደ መደበኛ ኑሮው እንዲመለስ ማድረግ ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ ስራ እንደሆነና ይህንንም የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል ፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ እና መከራ በቀላሉ በቃላት የሚገለጽ አይደለም ያሉት ዶክተር ጌታቸው፥ ችግሩን መረዳት የሚቻለው በቦታው ተገኝቶ ማየት ሲቻል ነው ብለዋል።

የአሸባሪውን የጭካኔ ድርጊቶች በማይካድራ፣ ቆቦ፣ ኮምቦልቻ፣ ጋሸና፣ ጋይንት፣ ጭና እና በሌሎች በርካታ አሸባሪው በገባባቸው አካባቢዎች ማየታቸውንና አሸባሪ ቡድኑ በፈጸማቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በጣም እንዳዘኑ ተናግረዋል፡፡

በርካታ ንጹሃን ከእነቤተሰቦቻቸው የዘር ማጥፋት በሚመስል መልኩ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል፤ እናቶችና ህጻናት ተደፍረዋል ፤ በርካታ መሰረተ ልማቶች የዝርፊያ እና ውድመት ሰለባ ሆነዋል ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳደሩ።

በአመለወርቅ ደምሰው

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.