Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ እና የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ስትራቴጂያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እና በቅርቡ የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሊዩ ጂያንቾኦ የዌብናር ውይይት አድርገዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ለቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሊዩ ጂያንቾኦ፥ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለ አረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ገለጻ አድርገውላቸዋል።

አቶ አደም ፋራህ በቻይና እየተመዘገበ ላለው ስኬት የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲን አመራር አድንቀዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲም ሀገር በቀል ፖሊሲዎችን በመተግበር ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሂደቱም ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ልምዶችን ሲቀስም መቆየቱንና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

አሁን በምንገኝበት ሀገራዊና ዓለማዊ ሁኔታ አንድነትንና ትብብርን ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት አቶ አደም፥ ሁለቱ እህት ፓርቲዎች ተግባር ተኮር የሆነ ግንኙነታቸውን በማጠናከር የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባቸው አውስተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መድረክም የባለብዙ ትብብር ማዕቀፎችን በማጠናከር ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በዓለም እንዲሰፍን ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ብልጽግና ፓርቲ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሊዩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ዋናዋ ምሰሶ እንደሆነች ቻይና እንደምታምን እና የብልጽግና ፓርቲም በቀጠናዊ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች አጋር እንደሆነ አመላክተዋል።

የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማሳደግ በቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ በኩል ጠንካራ ፍላጎት መኖሩን አንስተው የሁለቱን ፓርቲዎች የወደፊት የትብብር መስኮች ጠቅሰዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተስማሙ ሲሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችንም በቅርቡ እንደሚጀምሩ መግለጻቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.