Fana: At a Speed of Life!

የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዘመናዊ አገልግሎት ለመሥጠት እንደሚሰራ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሦስት ዓመታት የኢሚግሬሽን ፣ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር  በመሆን ሲያገለግሉ  የቆዩት አቶ ሙጂብ ጀማል የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር በመሆን አዲስ ለተሾሙት አቶ ብሩህ ተስፋ ሙሉጌታ በዛሬው ዕለት የሥራ ርክክብ አድርገዋል።

በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ፣ በቴክኖሎጂ ዘርፎችና፣ የኤጀንሲውን የአገልግሎት አሠጣጥ በማሻሻልና በማስፋፋት ረገድ ባለፉት ሶስት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውን የገለጹት አቶ ሙጂብ፥  ኤጀንሲው ከተገልጋይ ህብረተሰቡ ጋር ያለውን ቅርበት ለማሻሻል ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው የአገልግሎት አሠጣጡን ለማሻሻል ተቋሙ የሚመራበትን የስትራቴጂክ ዕቅድ ፣ ለሀገሪቱ የሲቪል ምዝገባ የሚያገለግል የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሰነድ እንዲሁም የኮሚኒኬሽን ዘርፍ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም አቶ ሙጂብ አመልክተዋል።

የኢሚግሬሽን ፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን የተሾሙት አቶ ብሩህ ተስፋ ሙሉጌታ በሥራ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፥ በቀጣይ ኤጀንሲው ለኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት ግልጽ ፣ ቀልጣፋ፣ ተዓማኒነት ያለውና እርካታ የተሞላበት ለማድረግ ከወዲሁ በቁርጠኝነት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም አገልግሎት ለማግኘት ወደ ኤጀንሲው የሚመጡ የሃገር ዉስጥ እና የውጭ ሀገር ዜጎችን የሚመጥን ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመሥጠት እንደሚሰሩ አያይዘው ገልጸዋል ።

በተጨማሪም ለወደፊቱ የኤጀንሲውን አሠራር ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ ጋር ተባብረውና ተቀናጅተው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ብሩህ ተስፋ  የኢሚግሬሽን ፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.