Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተቋቋመበት አላማ አንፃር ሃላፊነቶችን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተቋቋመበት አላማ አንፃር የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አድምጧል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ፥ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ 15 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ከዚህ ቀደም በነበሩ ፖለቲካዊ እና ተያያዥ ምክንያቶች የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በተገቢው መንገድ እየተወጣ አለመሆኑን አስታውሰዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ የማዋቀር እና የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት የተቋሙን አቅም እና ውስንነቶች እንዲሁም የሚስተዋሉ የህግ ማዕቀፍ ክፍተቶች እና ውስንነቶችን ማሻሻል የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት መደረጉን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ከወጣ 20 ዓመት በላይ ያለፈው መሆኑን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፥ አዋጁን አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሚዘጋጀው የማሻሻያ አዋጅም በተባበሩት መንግስታቱ ድርጅት በሚታወቀው እና የሁሉም ሀገራት ሰብዓዊ መብት ተቋማት በሚመሩበት ዓለም አቀፋዊ መርህ የሚቃኝ መሆኑንም አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት አላማ አንፃር የተጣለበትን ሃላፊነት በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

አዋጁ በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ወንጀል፥ በዜጎች አካል፣ ህይወት እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መከላከል የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ባላፈም ወንጀሉን ለመከላከል፣ ወንጀል ፈጻሚዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ፣ የተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋም በተለይም ለወንጀሎቹ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግና የተጎጂዎችን ዕድሜ፣ ጾታና ልዩ ፍላጎት ያማከለ ስራ መስራት እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.