Fana: At a Speed of Life!

የኢፌዴሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ-ግብረ ኃይል የጥምቀት በዓል በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ-ግብረ ኃይል የጥምቀት በዓል በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል የጋራ-ግብረ ኃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ስጋትና ችግር አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ-ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

ግብረ-ኃይሉ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከደብር ኃላፊዎች እንዲሁም ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም በዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቅ መቻሉን ነው  የገለጸው፡፡

ለበዓሉ ድምቀትና ስኬት መላው የሀገራችን ሕዝብ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከቱና የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ከማዕከል በሚሰጠው ትዕዛዝ ስራውን በአግባቡ በመምራቱ እንዲሁም የፀጥታ ስራውን ለማሳለጥ ቴክኖሎጂን በከፍተኛ ደረጃ በመጠቀም የፀጥታና የደህንነት አካላት የመፈፀም አቅማቸው በከፍተኛ ደረጃ ያደገበት ሁኔታ በመፈጠሩ እንደሆነም ታውቋል፡፡

በተጨማሪም የጋራ ግብረ-ኃይሉ በቅንጅትና በጠንካራ አመራር ከማዕከል በሚሰጥ ትዕዛዝ በመመራት እንዲሁም ችግር ያጋጥማል ተብሎ የተጠረጠሩ ቦታዎችን አስቀድሞ ለይቶ በማሰማራት በዓሉን በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል ብሏል፡፡

ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ሕዝበ ክርስቲያን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የደብር ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም በዓሉን ለማስተባበር በየደረጃው የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ግብረ-ኃይሉ የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታና ደህንነት የጋራ-ግብረ ኃይል ይህ ታላቅ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሌት ተቀን በመስራት ኃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡት የግብረ-ኃይሉ አባላት በሙሉ የላቀ ምስጋናውን ማቅረቡን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህንን በዓል የሀገራችንን ገፅታ በሚገነባ አኳሃን በስኬት ማጠናቀቅ መቻላችን ቀጣይም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ታላላቅ ሁነቶችን ብሎም መጪውን የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ጨምሮ ለማስተናገድ የተሟላ ብቃት ያለን መሆኑን ለማሳየት የተቻለበትም ነው ሲል ግብረ-ኃይሉ ጨምሮ ገልጿል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.