Fana: At a Speed of Life!

የክልልና የፌደራል የህግ አስከባሪ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንብና መመሪያ አፈፃፀምን ገመገሙ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል እና የፌደራል የህግ አስከባሪ አካላት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንብና መመሪያ አፈፃፀምን ገመገሙ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፥ ትናንት በተካሄደው በዚህ ግምገማ በአፈፃፀም ላይ ብዙ መሻሻሎች እና ውጤቶች መኖራቸውን እንዲሁም ብዙ ክፍተቶችም እንዳሉ ታይተዋል።

የአዋጁ እና የደንቦቹ አላማ ለመቅጣት ሳይሆን ህዝብን ከወረርሽኙ ለመታደግ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ አዳነች፥ የህግ ማስከበር ስራ ውጤታማነቱን የምናውቀው በተቀጡ ሰዎች ብዛት እና በቅጣቱ ክብደት ሳይሆን ወረርሽኙን ለመግታት ባደረግነው አስተዋአፆ መሆን እንዳለበት ተግባብተናል ነው ያሉት።

ህግ የማስከበር ስራ ላይ የማህበረሰባችን መዘናጋት፣ ችላ ማለት እና መላመድ በብዛት መታየቱንም ነው የጠቀሱት።

ለዚህም ሲባል ህግ አስከባሪ አካላት ብዙ የማነቃቃት ስራ መከናወን እንዳለበት ተረድቶ መጀመሪያ እራሳችውን ጠብቀው ለማህበረሰቡ ምሳሌ መሆን እንዳለባቸው መተማመን ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

ዓለም አቀፍ ወረርሽ የሆነው የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ስርጭቱን ለመግታት በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወቃል።

በሀገሪቱ እስካሁን 1 ሺህ 344 ሰዎች የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን፥ 14 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.