Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ  ለግንቦት 20 በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለግንቦት 20 በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ግንቦት 20 የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ከቀየሩ ዕለታት አንዱ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ለማድረግ አያሌ ታጋዮች እጅግ ውድ የሆነውን ህይወታቸው ሰውተዋል ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

የግንቦት 20 ታጋዮች የነፍስ ዋጋ የከፈሉለት ዓላማ ግፍና ጭቆና፣ አድሎና ወገንተኝነት ቆሞ፤ እኩልነት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መሆኑን በመልዕክታቸው አንስተዋል።

ግንቦት ሃያን ማክበር ያለብን እነዚህን ዓላማዎች እያሰብን መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀኑን የምናስበው በግንቦት ሃያ ላይ ተቸክለን ሳይሆን ወደፊት እየሄድን የኋላውን እየገመገምን መሆን አለበትም በማለት አሳስበዋል፡፡

ግንቦት ሃያን ያመጡ ታጋዮች ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ግንቦት ሃያ ሁለት መውሰድ እንጂ ወደ ግንቦት አሥራ ዘጠኝ መመለስ አልነበረምም ነው ያሉት፡፡

ሀገራቸው በሁሉም መመዘኛ ግንቦት ሃያን አልፋ ግንቦት ሃያ አንድንም ተሻግራ ወደ ግንቦት 22 መድረስ ነበር ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የግንቦት ሃያ ታጋዮችን ዓላማ የምናሳካው በሁለመናዋ ከግንቦት 19 የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ከቻልን ብቻ ነው፤ የብልጽግና ጎዳናችን ዓላማ ግንቦት ሃያ ላይ ቆሞ ግንቦት አሥራ ዘጠኝን እያሰቡ መኩራራት ሳይሆን ሀገራችንን ወደ ግንቦት 22 ማስፈንጠር ነው ሲሉም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ማለትም ሀገራችን ከነበረችበት አስከፊ ሁኔታ ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን መድረስ ወደነበረባት የላቀ ደረጃ ማድረስ መሆኑን አስታውሰዋል።

የግንቦት ሃያ የድል መታሰቢያ በዓልን ሰናከብር በተባበረ ክንድ ከግንቦት ሃያ የሚልቅ፣ ወደ ግንቦት 19 እንዳንመለስ የሚያደርግ ምጡቅ ሥርዓት ለመገንባት ቃላችን የምናድስበት እና ወደ ላቅ ውጤት ለመቀየር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምንገባበት መሆን ይገባዋል ብለዋል በመልዕክታቸው።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.