Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው በጥሬ ገንዘብ የተካሄደ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭና የብድር ውሎችን እንደማያስተናግድ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኤጀንሲው በጥሬ ገንዘብ ለተካሄደ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውልና የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት እንደማይሰጥ አስታወቀ።
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል እንዲሁም የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ላይ የአሰራር ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል።
በዚሁ መሰረት ከዛሬ መስከረም 07 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ኤጀንሲው ባደረገው የአሰራር ማሻሻያ መሰረት የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል እንዲሁም የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ኤጀንሲው የሚሄዱ ተገልጋዮች የሽያጭ ዋጋ ወይም የብድሩ ገንዘብ አከፋፈልን በተመለከተ ክፍያው መፈጸም ያለበት፦
• በሽያጭ ውል ጊዜ የሽያጭ ዋጋው ባንክ ከሚገኝ የገዢ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ሻጭ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ መሆን አለበት።
• በብድር ውል ጊዜ የብድሩ ገንዘብ ባንክ ከሚገኝ የአበዳሪ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ተበዳሪ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ መሆን አለበት።
በመሆኑም የሽያጩ ዋጋ ወይም የብድሩ ገንዘብ ክፍያው ከላይ በተገለጸው አግባብ የተፈጸመ ስለመሆኑ የሚገልጽና በባንኩ ማህተም የተደገፈ የሂሳብ ማስተላለፊያ የሰነድ ማስረጃ መቅረብ ያለበት መሆኑንም ኤጀንሲው አስታውቋል።
በተጨማሪም ህገወጥነትን ለመከላከል ሲባል ሌሎች የአሰራር ማሻሻያዎች እስኪደረጉ ድረስ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀ ንብረትን በስጦታ የማስተላለፍ ውል አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑንም ከፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.