Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ካርታ በይፋ ተመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የህዝብ ትራንስፖርትን ለማሻሻል ይረዳል ተብሎ የታመነበት የጉዞ እቅድ መተግበሪያ (ዲጂታል ማፒንግ) ይፋ ሆነ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ መፍትሄ ይዞ መንቀቀሳቀስ እንደሚገባ በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

ከከተማ መስፋፋት እና የህዝብ ቁጥር እያደገ መምጣት ጋር ተያይዞም የአዳዲስ አካባቢዎች እና መኖሪያ ሰፈሮች መፈጠራቸውን አንስተው፥ አዳዲስ የጉዞ መስመሮች መፈጠራቸውን እና በዚህ ሳቢያም የአውቶቡስና የታክሲ መስመሮችን ለማወቅ ብሎም ለመጠቀም ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍም ከናይሮቢ (ዲጂታል ማታተስ) እንዲሁም ካይሮ (የካይሮ ትራንስፖርት) ተሞክሮ በመውሰድ የአዲስ አበባን የህዝብ ትራንስፖርት የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ካርታ (ዲጂታል ማፕ) ላይ ማስፈር መቻሉን ገልጸዋል።

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በተለይም የህዝቡ የትራንስፖርት ተጠቃሚነትና የማጓጓዝ አቅም በየዓመቱ በአማካይ በ9 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተጠቅሷል።

ይሁን እንጂ የብዙሃን ትራንስፖርት አቅርቦቱ ካለው ፍላጎት አንጻር ውስን እንደነበር በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

የጉዞ መተግበሪያውን ለማከናወን በዋናነት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲቲዩት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን፥ የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር፣ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ የሸገር የብዙሀን ትራንስፖርት እና የከተማ የሚኒባስ ታክሲ የአገልግሎት መስመር መነሻ፣ የመተላለፊያ እና የመዳረሻ እና ፌርማታ አካባቢ ቦታዎች መረጃን በአካል ተገኝቶ በመሰብሰብ ለማካተት ተችሏል።

ዛሬ የተጀመረው የጉዞ እቅድ መተግበሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲቲዩት እና በየክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች እንደሚስፋፋ መገለጹን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.