Fana: At a Speed of Life!

ፊሊፒንስ የአውሮፓ ህብረት ስለኢትዮጵያ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተቀባይነት የለውም አለች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተፈጽሟል በሚል ሊነጋገርበት ቀጠሮ የያዘለት የውሳኔ ሃሳብ በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው በጄኔቫ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፊሊፒንስ ቋሚ መልዕክተኛ ኤቫን ጋርሽያ ገለጹ።
 
የፊሊፒንስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዮዶር ሎሲን በኢትዮጵያ ተፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለማጣራት የሚቋቋመው አለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን ዋነኛ ዓላማ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሳይሆን በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትና ሉዓላዊነትን የመደፈር ፍላጎት አድርገን እንወስደዋለን ብለዋል።
 
የዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች ፍላጎታቸው ጣልቃ ለመግባት ከመሻት የመነጨ ፖለቲካዊ ፍላጎት መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያመላከቱት።
 
ሚኒስትሩ አክለውም “የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን በመረዳት የማስተካከያ እርምጃዎችን እንደሚወስድና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት፥ ጥናት የተደረገበትን ተመሳሳይ አጀንዳ አንስቶ የውሳኔ ሃሳብ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ሉዓላዊነትን ከመጣስ ውጪ ምን ሊሆን ይችላል? ምንስ አዲስ ነገር ያመጣሉ?” ሲሉም ጠይቀዋል።
 
“የውሳኔ ሀሳቡ ለጉዳዩ አቀንቃኞች የተሳሳተ ተግባርን ትክክል የመሆን ስሜት ከመፍጠር ባሻገር የሚያመጣው ለውጥ የለም” ያሉት ሚኒስትሩ÷ “እ.ኤ.አ በ2019 ፊሊፒንስም በእጽ አዘዋዋሪዎች ላይ ተፈጸሙ በተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስሟ በአስመሳዮች ሲጠፋ ነበር” ሲሉ ማስታወሳቸውን ኒውስ ኤቢኤስ በድረ ገጹ አስነብቧል።
 
ሉዓላዊነትን ለመጣስ በማሰብ ጉዳዩን ከተገቢው በላይ በመለጠጥ የሚያራግቡ ሀገራት ራሳቸው በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የሚፈጸሙባቸውና ለችግሮቻቸው መፍትሄ ያላስቀመጡ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
 
ሀገራቱ የግል ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅና የራሳቸውን ጥፋቶች ለመሸፋፈን የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱን ከመጠቀም ሊቆጠቡ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
 
ተመሳሳይ ጉዳዮች እየተነሱ የሚወድቁበትና ያለ ፍርድ ሂደት ሀገራት ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት፣ የሀገራት ሉዓላዊነት የሚደፈርበት፥ ብሎም ለውይይት በር የሚዘጋው ይህ ዓይነቱ ኢፍትሃዊ አካሄድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤቱን አቅም የሚያዳክም ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በመሆኑም ይህ አካሄድ ካልተስተካከለ በስብሰባው ላይ የምትታደመው ፊሊፒንስ በተቃውሞ እንደምትወጣ አሰቀድመው ማስጠንቀቃቸውን መረጃው አስታውሷል።
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.