Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በቆየባቸው ጊዜያት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል- የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኑ የአማራን ክልል በወረረበት ወቅት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንና ዝርፊያ መፈፀሙን የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን ጣሰው ገለጹ፡፡
የአሸባሪ ቡድኑ ወደ ክልሉ በገባበት ወቅት÷ የመካከለኛና ዝቅተኛ መስመሮችን ጨምሮ ትራንስፎርመሮችን እና ሌሎች የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በደቡብ ጎንደር፣ በደብረ ብረሃን እና በደሴ አካባቢዎች ወረራ ባደረገበት ወቅት በኤሌክተሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱም በላይ፥ ተሸከርካሪዎችን፣ ትራንስፎረመሮችን፣ ኮምፒውተሮችን፣ ፕሪንተሮች እና ሌሎች የቢሮ መገልገያ መሳሪያዎችን ማውደሙንና መዝረፉን አብራተዋል፡፡
በደሴ ዲስትሪክት ብቻ ከ80 በላይ ትራንስፎርመሮች፣ 12 ተሽከርካሪዎች፣ ከ120 በላይ ኮምፒውተሮችን፣ ከ30 በላይ ፕሪንተሮች፣ የስድስት ተሽከርካሪ የአካል ክፍሎችን እና ሌሎች በርካታ ንብረቶች በሽብር ቡድኑ መዘረፋቸውን አቶ ሰለሞን አረጋግጠዋል።
በጦርነቱ የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ለማወቅ በተደረገ ጥናት÷ በደቡብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ሁለት ማዕከላት 2 ሚሊየን 447 ሺህ 747 ብር፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ዲስትሪክት ስር በሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት 19 ሚሊየን 429 ሺህ 498 ብር እና በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዲስትሪክት ስር በሚገኙ ማዕከላት የውጫሌና ወገልጤናን ሳይጨምር 15 ሚሊየን 206 ሺህ ብር ግምት ያለው ውድመት ደርሷል ተብሏል፡፡
በሶስቱም አካባቢዎች ከ37 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውድመት መፈጸሙ ተረጋግጧል ብለዋል አቶ ሰለሞን፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በፀጥታ ሃይሎች እየተሸነፈ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች እየለቀቀ ሲሄድ፥ የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራርና ሰራተኞች እግር በእግር እየተከታተሉ የወደሙ የኤልክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትክ ሃይል እንዲመለስና ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ሌት ተቀን ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለፁት ስራ አስፈጻሚው፥ ስራው በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡
ስራ አስፈጻሚው በወልዲያ ዲስትሪክት ስር በሚገኙ የሰሜን ወሎና የዋግኽምራ ዞን አካባቢዎች የደረሱ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትና የንብረት ውድመት የሚለይ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰለሞን፥ ጥናቱ እንደተጠናቀቀም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ማለታቸውን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.