Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የሚገኙ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ሕወሓት የፈጸመውን ወረራ ተከትሎ የቀረበውን የህልውና ትግል ጥሪ ለመደገፍ መደበኛ አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ከህልውና ትግሉ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ከተወሰኑ ተቋማት በስተቀር ሁሉም በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አገልግሎታቸውን አቋርጠው የህልውና ትግሉን በተለያየ መልኩ ሲደግፉ መቆየታቸውን የቢሮ ኃላፊው ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ የህልውና ዘመቻው መልክ እየያዘ ስለሆነና አብዛኞቹ ቦታዎችም ከወረራ ነጻ ስለወጡ ሁሉም ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡
ከውስን ቦታዎች ውጭ አብዛኞቹ አካባቢዎች ከወራሪው ቡድን ነጻ የወጡ በመሆኑ፥ የክልሉ ምክር ቤት አጠቃላይ ሁኔታዎችን ገምግሞ ውሳኔው እንዲቀየር ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ግዛቸው፥ ውሳኔው ታሳቢ ያደረገውም ሌሎች ሥራዎች እንዳይጎዱና ኢኮኖሚውም እንዳይቀዛቀዝ በሚል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሁሉም የመንግሥት ተቋማትና ሠራተኞች ከመደበኛ ተግባራቸው ጎን ለጎን የህልውና ዘመቻውን መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ መጠየቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ተይዘው የቆዩ አካባቢዎች ብዙ ነገራቸው የተጎዳ በመሆኑ ሠራተኞች ድሉን የበለጠ ለማጠናከርና ጉዳቱን ሊያካክስ በሚችል ሞራልና ተነሳሽነት ሥራ መጀመራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፥ በቀጣይም በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚው ዘርፍና በማህበራዊ ዘርፍ ያሉ ሥራዎች ላይ ክልሉን ሊለውጥ በሚችል ደረጃ እንደተቀጣሪ ሳይሆን የባለቤትነት ስሜት ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የክልሉን ሠላምና ፀጥታ ለመጠበቅና ህብረተሰቡን በሁሉም መስክ ለመለወጥ በሚሰራው ሥራ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ሚና ትልቅ በመሆኑ ሁላችንም የተጣለብንን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.