Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው ለእናት አገሩ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ የበይነ-መረብ ውይይት ተደረገ።

በውይይቱ በኬንያ፥ ማላዊ እና ሲሸልስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገራት እና ኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍስሃ ሻውል እንዲሁም በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ግርማ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ገለፃዎች ተደርገዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ልዩ መልክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በፕሮግራሙ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ÷ አገራችን በኬንያ፣ ማላዊ እና ሲሸልስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው እያደረጉ ለሚገኙት የገንዘብ፣ የዓይነት እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ፈተና በጋራ ለመወጣት ዳያስፖራው ዘርፈ-ብዙ አስተዋጽኦ እንዳለውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያቀረቡትን የ1 ሚሊየን የዳያስፖራ አባላት ወደ አገር ቤት ጥሪን ተከትሎ ኤምባሲው እና ለዚህ ጉዞ መሳካት በአገር ቤት በተቋቋመው ኮሚቴ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ በመጥቀስ በኬንያ፣ ማላዊ እና ሲሸልስ የሚገኙ ወገኖቻችን ጥሪውን ተቀብለው በፕሮግራሙ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጋብዘዋል።

አምባሳደር ፍስሃ ሻውል በበኩላቸው፥ ላለፉት ሶስት ዓመታት እየተካሄደ በሚገኘው የለውጥ ሂደት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሲያራምድ የነበረውን ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አቋም እና የአገራችን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል የፈፀማቸውን የሽብር ድርጊቶች ፤ በቅርቡም የህወሓት ቡድን ወደ አዲስ አበባ በመግባት ላይ መሆኑንና ኢትዮጵያን ሊያፈርስ እንደሆነ ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲነዛ የነበረው የሀሰት ዜና ዜጎችን ለድንጋጤ የዳረገ እንደነበር እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግንባር ድረስ በመገኘት አመራር በመስጠት ያሳዩት ቁርጠኝነት ለብዙሃን ስላሳደረው ተስፋ እንዲሁም የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ዓላማውን ስላደረገው ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲን በመወከል ገለፃ ያደረጉት አቶ ወንድወሰን ግርማ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኢትዮጰያ ዳያስፖራ የሶስት ዓመታቱ ለውጥ ባለቤት መሆኑን በመጥቀስ ፥ ለአገር መከላከያ እና ለተጎዱ ወገኖቻችን በገንዘብና በዓይነት ያበረከተው አስተዋፅኦ እጅግ የሚመሰገን መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም ÷ ‘‘ህወሓት የአገራችንን ሉዓላዊነት ከደፈረ ጀምሮ በተመድ የፀጥታው ም/ቤት በታላቁ የህዳሴ ግድብ እና ፀጥታ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ቢደረጉም በአገራችን ላይ የታሰበውን ያህል ጫና ለማድረግ አለመቻሉን፣ በዚህም የዳያስፖራው ትግል እና የአገራችን የዲፕሎማሲ ጥረት የጎላ ድርሻ አላቸው’’ ብለዋል።

በሌላ በኩል በኬንያ እና ማላዊ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የኮሚኒቲ አደረጃጀት እና በኢትዮ – ኬንያ ወዳጅነት ማህበር ተወካዮች በሰጡት አስተያየት ÷ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና በጋራ ለመወጣትና ማንኛውንም የገንዘብ እና የሙያ ድጋፍ ለማድረግ ሁልጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን እንደገለፁ በኬኒያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.