Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በአሸባሪው ወረራ ስር በነበሩ ዞኖች ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ ዞኖች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡
 
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት÷በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራና ውድመት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ የመገንባት ሥራ እየተካሄደ ነው።
 
የሽብር ቡድኑ ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመባቸው ሰባት ዞኖችና አንድ ከተማ አስተዳደር ጭካኔ የተሞላበት ዘረፋና ውድመት አድርሷል ሲሉ አወስተዋል።
 
በክልሉ ለመስማት የሚከብዱ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳቶችን በማድረስ በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ከፍተኛ የጥፋት ተግባር መፈጸሙን አስረድተዋል።
 
የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከ11 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለችግር ማጋለጡን አመልክተዋል።
 
አሸባሪው ሃይል በጦርነቱ ተሸንፎ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ ከወጣ በኋላ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስተባባሪው ገልጸዋል።
 
በተለይም ለህዝብ ግልጋሎት የሚሰጡ ተቋማት ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
 
በየአካባቢው መደበኛ የሰላም ማስከበርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራም እንዲሁ።
 
ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ባሉበት አቅም ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ያልተቆጠበ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪን በመቀበል ወደ ሀገራቸው የሚመጡ ዳያስፖራዎች በመልሶ ማልማትና ማቋቋም ሥራው የበኩላቸውን እንዲወጡ የማመቻቸት ስራ እንደሚካሄድ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም፣ የወደሙ ተቋማትን ወደ አገልግሎት የማስገባትና ሌሎች ሥራዎች በመንግስት አቅም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ መላው ህዝብ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.