ሩሲያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ለኢትዮጵያ ያላትን ወዳጅነት በማሳየቷ ቋሚ ኮሚቴው አድናቆቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሩሲያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ለኢትዮጵያ ያላትን ወዳጅነት በማሳየቷ አድናቆቱን ገለጸ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በዛሬው ዕለት ከሩሲያ አምባሳደር ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርጓል፡፡
የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ባደረጉት ንግግር፥ ሁለቱ አገራት ባላቸው የረዥም ጊዜ ግንኙነት ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ሩሲያ ከጎኗ የምትሰለፍ ወዳጅ አገር መሆኗን ገልፀዋል፡፡
ዶክተር ዲማ አክለውም ፥ ሩሲያ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች በምትሰጠው የትምህርት እድል በርካታ ኢትዮጵያውያን ተምረው በመምጣት አገራቸውን እያገለገሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ እስካሁን ድረስ ያደረገችውን ትብብር በማጠናከር በቀጣይም ኢትዮጵያ ለምታደርገው የልማት እንቅስቃሴ ድጋፏን እንድትቀጥል የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደሩን ጠይቀዋል፡፡
የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጊኒ ቴሬክሂን በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ እንዳስቆጠረ ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ግንኙነትና ወዳጅነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ለቋሚ ኮሚቴው ማረጋገጣቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት እና የአሁኑ አፍሪካ ህብረት የቆድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አገር መሆኗን የገለጹት አምባሳደሩ ፥ ኢትዮጵያና ሩሲያ የተፈራረሟቸው ሁለት ስምምነቶች በምክር ቤቱ ጸድቆ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴውን ጠይቀዋል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የኢትዮጵያና የሩሲያ ምክር ቤቶች በወዳጅነት ኮሚቴ በኩል የነበራቸው ግንኙነት የተጠናከረ እንደነበር ጠቁመው፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ግን የተቀዛቀዘ በመሆኑ የወዳጅነት ኮሚቴው መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!