Fana: At a Speed of Life!

ለመኸር ምርት የሚሆኑ ግብአቶችን ከሕጋዊ አሰራር ውጪ የሚሸጥ አካል ላይ እርምጃ ይወሰዳል-የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ 2014/15 የምርት ዘመን የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ ማስገባት መጀመሩን የግብርና ሚኒስር አስታወቀ።
እስካሁን ከ 60 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንና ተጨማሪ ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦችም ወደ ጅቡቲ ወደብ እየደረሱ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
ለቀጣይ የመኸር የምርት ዘመንም 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እቅድ መያዙን ጠቁመው፥ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ቀድመው ማዳበሪያ የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ላይም ከባለፈው ምርት ዘመን የተረፈ ማዳበሪያን እንዲጠቀሙ የማድረግ አማራጭም መቀመጡንም ነው የገለጹት።
የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ከማድረስ በተጨማሪ የምርጥ ዘር አቅርቦትም ትልቅ ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመው፥ የምርጥ ዘር አቅርቦቱ በየአመቱ መጠኑ እየጨመረ ቢሄድም ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለሆነ መመጣጠን አልቻለም ብለዋል፡፡
በዚህም ምርጥ ዘሩ በሀገር ውስጥ የሚመረት በመሆኑ የምርምር ማእከላትን በመጠቀም እና በመስኖ በስፋት በማምረት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለቀጣዩ የምርት ዘመንም 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ለማድረስ መታቀዱን የገለጹት ዶክተር ሶፊያ ÷ ለ2014/15 የመኸር ምርት ዘመን የሚሆኑ ግብአቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ ግብአቶቹ በሚወጣላቸው ዋጋ በማይሸጡ እና ከሕጋዊ አሰራር ውጭ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
ለዚሁ አሰራር እንዲረዳም ከክልሎች ጋር በየጊዜው ስራዎች እየተገመገሙ እና ያሉ ችግሮችም እየተለዩ ነው ብለዋል።
ለቀጣይ የመኸር ጊዜ የታሰበው የአፈር ማዳበሪያ እስከ 4 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ እንሚገባም የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ተናግረዋል።
በዙፋን ካሳሁን
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.