Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ720 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአደገኛና መጤ አረም ተይዟል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከ720 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአደገኛና መጤ አረም መያዙን የአማራ ክልል የእፅዋት ዘርና ሌሎች ግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ኳራንታይን ገለፀ።

የክልሉ የእፅዋት ዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ቁጥጥር ኳራንታይን ባለስልጣንና የሜዳ ፕሮጀክት ትብብር፥ በአደገኛና መጤ አረም መከላከልና ፀረ ተባይ ኬሚካል ጥራት ቁጥጥር አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ በክልሉ እንቦጭ አረምን ጨምሮ 12 አደገኛና መጤ አረም መኖሩን የፀረ ተባይ ኬሚካል፣ ማዳበሪያና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ሞገስ ዘውዱ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች 720 ሺህ 424 ሄክታር መሬት በአደገኛና መጤ አረም መያዙን በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።

አደገኛና መጤ አረም በሀገር አቀፍ ደረጃ 30 በመቶ ምርትና ምርታማነትን የሚቀንስ እና በጤና እንዲሁም በነባር የሀገር ውስጥ ዝርያ ተክሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም አስረድተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለአደገኛና መጤ አረም በክልሉ መንግስት የተሰጠው ትኩረት ማነስ፣ ባለድርሻ አካላት የመከላከል ስራውን ለግብርና ቢሮ ብቻ መተዋቸው እና የቅንጅት ስራ አለመኖር አረሙ እንዲስፋፋ ማድረጉን አንስተዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶክተር ሰለሞን እንዳሉት፥ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ አደገኛና መጤ አረም የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ቢሰራም የቅንጅት እና የትኩረት ማነስ ችግሮች በመኖራቸው የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም።

ችግሩን ለመቅረፍም ከአባባቢ ጥበቃ፣ ከመሬት አስተዳደርና ከኳራንታይን ባለስልጣን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.