Fana: At a Speed of Life!

ከ200 በላይ የመንግስት አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባበለጸጋቸው ስርዓቶች ውስጥ የሚተገበሩ 222 የመንግስት አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ መሆኑን አስታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር አገልግሎቶቹ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲተገበሩ ለማድረግ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የመንግስት አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግና የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ 2 ሺህ 500 አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት እቅድ መያዙን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ አሁን ላይ 222 አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከ100ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችም መመዝገባቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።
በትላንትናው ዕለትም 45 የመንግስት አገልግሎቶች ኦንላይን ለመስጠት የሚያስችሉ ስርዓቶች ለምተው መመረቃቸው ተመላክቷል።

በዚህ ዓመት 400 የመንግስት አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።

የመንግስት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት የሚሰጥበትን ፖርታልም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ሰዎች እንደጎበኙት መገለጹን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.