Fana: At a Speed of Life!

በ“ኢድ እስከ ኢድ ጥሪ” ዳያስፖራው በስፋት እንዲሳተፍ ሚሲዮኖች የጀመሩትን ንቅናቄ ሊያጠናክሩ ይገባል – አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ”ኢድ እስከ ኢድ ጥሪ” ዳያስፖራው በስፋት እንዲሳተፍ ሚሲዮኖች የጀመሩትን የዳያስፖራ ንቅናቄ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አሳሰቡ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የኢድ እስከ ኢድ ጥሪ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ጥምር ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ይህን ያሉት÷ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪን እንዲያስተባብር የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ከኢፌዱሪ ሚሲዮኖች ጋር የበይነ መረብ ውይይት ባደረገበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
በመልዕክታቸውም ሚሲዮኖች በመጀመሪያው ዙር የታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ ለታየው ሰፊ የዳያስፖራ ተሳትፎ ስላከናወኑት ስራ አመስግነው÷ ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪም በስኬት እንዲጠናቀቅ የጀመሩትን የዳያስፖራ ንቅናቄ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢድ እስከ ኢድ ጥሪ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ጥምር ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው÷ ጥሪው ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ያላትን ሚና ለዓለም ለማሳየት መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ከጥሪው ጋር በተያያዘ የተዘጋጁ እንደ ታላቁ የኢድ ስግደት የመሳሰሉ ሁነቶችን በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ውስጥ እንዲመዘገቡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ጥሪው ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅና የተዛባ ምስሏን ከማደስ እንዲሁም ህብረትን ከማጠናከር አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያስገነዘቡት ደግሞ÷ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኢድ እስከ ኢድ ጥሪ ብሔራዊ ኦፐሬሽናል ኮሚቴ ሴክሬታሪያት ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ናቸው፡፡
ጥሪው የአሰራር ቀጣይነትን፣ በተቋማትና በዜጎች እንዲሁም በወዳጆች ላይ ያለ እምነትን የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አምባሳደሮችና የሚሲዮን መሪዎች÷ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል።
ከአየር ትኬት የዋጋ ቅናሽ፣ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ ስለሚደረግባቸው መንገዶች፣ የኢትዮጵያ ወዳጆችን የተሳትፎ ፍላጎት ማበረታታት ስለሚቻልባቸው አማራጮች ውይይት መደረጉን ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ምላሽ የሚሹ ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግም ተገልጿል።
ዳያስፖራውም በራሱ በመደራጀትና ከሚሲዮኖች ጋር በቅርበት በመስራት ስኬታማ የሀገር ቤት ጉዞን እውን እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.