ኢመደአ እና የአማራ ባንክ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና የአማራ ባንክ በሳይበር ደኅንነትና መሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬ እለት ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን ሶካ ÷ አስተዳደሩ የሀገሪቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ተግቶ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆናቸው ለሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በተለይ ከባንኮች ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ባንክ ÷ የገንዘብ ተቋማት ለሳይበር ጥቃት ያላቸውን ተጋላጭነት ተገንዝቦ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ጋር ለመስራት ዝግጅነቱን ማሳየቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል ።
ባንኩ በሰው ኃይል እና ፖሊሲ የቴክኖሎጂ ድጋፎችን እና ትብብሮችን ለማድረግ የሚያስችለውን የውል ስምምነት መፈረሙ ለሌሎች ባንኮችም በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
የአማራ ባንክ ፕሬዝደንት አቶ ሄኖክ ከበደ በበኩላቸዉ ÷ ባንካቸው የፋይናንስ ሥራውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በርካታ ስራዎችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የምናገኘው ሙያዊ እገዛም ለባንኩ ሥራ ስኬት እና ዕድገት አጋዥ ይሆናል ነው ያሉት።
በስምምነቱ መሰረት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ÷ በሳይበር ደኅንነት ፣ በአይሲቲ አግልግሎት እና አስተዳደር ላይ የማማከር፣ የሳይበር ደኅንነት ኦዲት ስራ የመስራት፣ በአይቲ ስትራቴጂና ፍኖተ ካርታ፣ ፖሊሲ ማልማት ፣ በሳይበር ደኅንነት ላይ በሚዘጋጁ መመሪያዎች እና ደንቦች ላይ የማማከር ስራ የሚሰራ ሲሆን የቴክኒክ ስልጠናዎችንም ለባንኩ ባለሙያዎች ይሰጣል መባሉን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።