Fana: At a Speed of Life!

ክልሎች በቀጣይ የሚከበሩ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች በመጪዎቹ ቀናት የሚከበሩት የፋሲካና የዒድ አልፈጥር በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታወቁ፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በዓላትን ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ በመለየት፣ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል።

የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል እና ትራፊክ የመንገድ ደኅንነት ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው በሰጡት መግለጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመከላከል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ሊፈጠሩ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችን በመለየት ከኅብረተሰቡ ጋር በመናበብ ቅንጅታዊ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ የሐሰተኛ የብር ኖት ዝውውር፣ የትራፊክ አደጋ፣ የጥይት ተኩስ፣ ሕገ ወጥ የግብይት እንቅስቃሴ፣ የሰርጎ ገቦችን ጥፋት መከላከል ላይ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የፋሲካና የኢድ አልፈጥር በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሠራታቸውን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

የደቡብ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ በሠጡት መግለጫ ፥ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ከማህበረሰቡ ጋር ተጣምሮ ይሠራል ብለዋል፡፡

በተለይ የፀጥታ ችግር ባለባቸው የክልሉ አካባቢዎች፥ ነዋሪው በዓሉ በአብሮነትና በሰላም እንዲያከብር የፀጥታ ኃይሉ የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በገበያ ቦታዎች የሚደረጉ የምርት ማጭበርበርና ህገ ወጥ የገንዘብ ልውውጥን ለመቆጣጠር ማህበረሰቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም በሀረሪ ክልል ሰላምን ከማረጋገጥ አንፃር ህዝቡ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጠይቋል፡፡

በክልሉ የፋሲካ እና ዒድ አልፈጥር በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ቢሮው ተናግረዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥላሁን ዋደራ እንደገለፁት ፥ በክልሉን እየተስተዋለ የሚገኘውን አንፃራዊ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታ ሃይሉ ከህዝብ ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የፋሲካ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማስቻል አንፃርም አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፥ የዒድ አልፈጥር እና በክልሉ በልዩ ሁኔታ የሚከበረውን የሸዋል ዒድ በዓላት በሰላም እንዲከበሩና ለበዓላቱ የሚመጡ እንግዶች የተሳካ ቆይታ እንዲያደርጉም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ማላከታቸውንም ከየክልሎቹ ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ምንጭ፡- አሚኮ፣ የደቡብ እና ሐረሪ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤቶች

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.