Fana: At a Speed of Life!

74 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በአባአላ መንገድ በኩል ወደ መቀሌ ከተማ እየተጓዙ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 15 ፣ (ኤፍ ቢ ሲ) በሶስተኛው ዙር በዛሬው እለት 74 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በአባአላ መንገድ በኩል ወደ መቀሌ ከተማ እየተጓዙ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ÷የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ የገባውን ቃል በማክበር ምቹ የሰብዓዊ ርዳታ ማጓጓዣ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብሏል።

በዚህም መሠረት በሶስተኛው ዙር በዛሬው እለት 74 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በአባአላ መንገድ በኩል ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ እየተጓዙ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 6 ተሽከርካሪዎች ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች መሆናቸው ነው የተገለጸው።

መንግስት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እንዲደርስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያለው መግለጫው።

የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ወስጥ የሚገኙት የክልሉ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ወራሪው ሃይል አሁንም ከያዛቸው የአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች እንዲወጣና ምቹ የእርዳታ ማስተላለፊያ መስመርን መዘርጋት እንዲቻል የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ጥሪ ቀርበዋል፡፡

በተጨማሪም ወራሪው ሃይል ከሚነዘቸው የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች እንዲቆጠብ እና እስከአሁን ድረስ ያልተመለሱ 1ሺህ 25 ተሽከርካሪዎች በፍጥነት እንዲመለሱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.