Fana: At a Speed of Life!

በሐረር በአንድ ሆቴል ውስጥ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው – የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረር ከተማ ልዩ ስሙ ሸንኮር ቀበሌ 09 በአንድ ሆቴል ውስጥ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት አራት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘከሪያ ጥቃቱን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ÷ በትንሳኤ ዕለት እሁድ ከምሽቱ 2:45 ላይ በሸንኮር ወረዳ ቀበሌ 09 ዮድ ተብሎ በሚጠራው ሆቴል ላይ ማንነታቸው ለጊዜው ያልታወቀ ግለሰቦች በወረወሩት ቦምብ በስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
የጥቃቱ ሰላባ ከሆኑት ስምንት ግለሰቦች መካከል አራቱ መጠነኛ ሕክምና ተደርጎላቸው ወዲያው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ጠቁመው÷ ቀሪዎቹም በአስጊ ሁኔታ ላይ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ጥቃቱን በተመለከተ ኃላፊነት የጎደላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ከእውነታው በራቀ እና በምርመራ ላይ ያለን ጉዳይ÷ ባሻቸው መልኩ በማቅረብ ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ እንደሚገኙ በመግለጫቸው አንስተዋል።
ጠብ አጫሪ በሆነ መልኩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የሚያጋሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን የሐረሪ ክልል ብዙኃን መገናኛ ዘግቧል፡፡
ፖሊስ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ÷ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ አራት ግለሰቦች ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን የምርመራ ውጤቱ እንደተጠናቀቀ ለህብረተሰቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.