“በመስጠታችን እንባረክ ይሆናል እንጂ አይጎድልብንም” -ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አስተዳደሩ መጪውን የኢድአልፈጥር በአልና የረመዳን ፆም ፍቺ ምክንያት በማድረግ ከከተማ እስከ ብሎክ ድረስ 101ሺህ 480 ዜጎች ማዕድ አጋርቷል፡፡
ይህ የማእድ ማጋራት መረሀግብር፤ ከተባባሪ አካላት ጋር በሚደረግ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት በዘላቂነት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል።
ከንቲባ አዳነች በእኛ ኢትዮጵያውያን መካከል አንተ ትብስ በሚል የቆየውን የመከባበርና የመደጋገፍ እሴቶቻችንን በተግባር በመጠቀም ድጋፍ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እርብርብ ማድረግ ይገባናል ብለዋል ፡፡
በመስጠታችን እንባረክ ይሆናል እንጂ አይጎድልብንም እንዲሁም ወንድማማችነትና አብሮነታችን ይጠነክራልም ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
በዚሁ ወቅት ከንቲባዋ ከተማ አስተዳደሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚሰራቸው ስራዎችና በሚፈጥራቸው የሥራ ዕድሎች ሁሉ በመሳተፍ መንግስት እናንተን ለመደገፍ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ኑሯችሁን በዘላቂነት ለመቀየር መዘጋጀትና ማንኛውንም ስራ ለመስራት መወሰን ይኖርባችኋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አስፋው ተክሌ በበኩላቸው እኔነትን በመተው፣ እኛነትን በመምረጥ ሕዝባዊ አንድነታችንን በማጽናት ወደ ፊት እየተደጋገፍን በአብሮነት መሻገር እንዲቻለን የነበሩንን አጠቃላይ በጎ ማሕበራዊ ዕሴቶቻችንን ወደ ተግባር እየለወጥን መደጋገፍ ይኖርብናል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከሚያዚያ ወር የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ ሲደረግ በቀየው የማዕድ ማጋራት መርሀግብር የዛሬውን ጨምሮ 341ሺ 480 ድጋፍ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ተደርጓል የተባለ ሲሆን÷ የከተማዋ ባለሃብቶችም በከፍተኛ ሃገራዊ ስሜት ምለሽ እየሰጡም ነው መባሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡