በሸበል በረንታ ሙሽራ ሊያመጣ ሲጓዝ በነበረ መኪና ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሦስት ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ መርገጭ ንዑስ ሞዠንና አካባቢው ቀበሌ ኮሸሽላ ጎጥ ሙሽራ ለማምጣት እየተጓዘ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ረዳቱን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት አስታወቀ፡፡
የወረዳው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ዮሐንስ በላይ እንደገለጹት÷ አደጋው የተከሰተው ከመጠን በላይ ሰው በመጫኑና ያለአግባብ ”ከኮርቶ መጋላው” ላይ ተጭነው የነበሩት ሰዎች ለመዝለል ባደረጉት ሙከራ ነው፡፡
ትናንት ከቀኑ 10:00 ሰዓት አካባቢ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪው ሞዠንና አካባቢው ቀበሌ ኮሸሽላ ጎጥ ሲደርስ ወደ ኋላ ተንሸራቶ እረዳቱን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በአምስት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የሸበል በረንታ ወረዳ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡