Fana: At a Speed of Life!

ለትውልዱ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማውረስ እንዲቻል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምናስመዘግባቸው ድሎች በሚፈጥሩልን ወኔ ተበረታትተን በመሻገር ለትውልዱ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማውረስ እንድንችል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ ጥረታችን ኢኮኖሚው ተግዳሮቶችን ከመቋቋም አልፎ ወደማሸነፍ የሚያሸጋግር መሆን እንዳለበት ጠቁሞ፥ መንግሥት፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ፣ ምሁራንና ሕዝቡ፣ ሁሉም የየድርሻቸውን መወጣት ከቻሉ በእርግጥም ጥረታችን ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም ብሏል።
በየጊዜው እያደገ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቀነስ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተነድፈው ሲሰራባቸው ቆይተዋል ያለው መግለጫው÷ ባለፉት 9 ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚልየን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጿል።
የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

 

የ2014 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የኢኮኖሚ አፈጻጸምን በማስመልከት፣ ከብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሀገራችን ኢኮኖሚ እንደ ፖለቲካው ሁሉ በተለያዩ ምክንያቶች ለተደጋጋሚ ፈተናዎች ሲዳረግ ቆይቷል።
ያልተጠበቁ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የፈጠሯቸው ጫናዎች እጅግ ፈታኝ መሆናቸው አይካድም። የሰሜኑ ጦርነት ያስከተለው የንግድና የቢዝነስ እንቅስቃሴ መስተጓጎል እንዳለ ሆኖ የፈጠረው የመሰረተ ልማቶች ውድመትና የዜጎች መፈናቀል፣ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ቀውስ በኢኮኖሚያችን ላይ ያሳደረው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።
በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠመው ድርቅ እና እሱን ተከትሎ ባጋጠመው የሕዝብ ርሃብና የእንስሳት ሞት ኢትዮጵያን ብዙ አሳጥቷታል። ያም ሆኖ ግን የሀገራችን ኢኮኖሚ የሀገር ውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁሞ በተሻለ ሁኔታ በመጓዝ ላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤቱም የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሁኔታዎች በገመገመበት ወቅት ያረጋገጠው ይሄንን ነው።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሩብ ዓመታት ላይ የተመዘገበው ዕድገት ላይ በመንተራስ የዓመቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በአማካይ በ6.6% ዕድገት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን፥ ይኽ ዕድገት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሬ አለው።
ለዚህ ዕድገት መመዝገብ በዋነኝነት በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሰብል ምርት ላይ የታየው እመርታ ተጠቃሸ ነው።
የመኸር ምርት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የበጋ ስንዴን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን ተከትሎ 613 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ25 ሚልዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል። ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ቀስ በቀስ እያገገመ የሚገኘው የአገልገሎት ዘርፉ ላይ ተስፋ ሰጪ ዕድገት እየታየ ነው።
በተመሳሳይ መጠነኛ የዕድገት መቀነስ የተመዘገበበት የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደገና እንዲያንሠራራ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል። በጦርነቱ ተቀዛቅዞ የቆየውን የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ድርሻ ለማሳደግ የተደረጉ ርብርቦች ውጤት ማምጣት ጀምረዋል።
ከኢንቨስትመንት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው የብድርና ቁጠባ መጠንም ላይ ጭማሪዎች የተመዘገቡበት ወቅት ነበር፡፡
የባንኮች አጠቃላይ የቁጠባ መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ25% በማደግ 1.6 ትሪልዮን ብር ደርሷል፤ ይህም ከፍተኛ ብድርን ለግሉ ዘርፍ ማቅረብ እንድንችል አድርጎናል። ከውጭ ንግድ 2.95 ቢሊየን ዶላር የተገኘ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 2.05 ቢሊየን ዶላር በሆነ ድርሻ አሁንም ግብርናው የወጪ ንግዱ የጀርባ አጥንት ሆኖ ቀጥሏል።
ከግብርናው በመቀጠል የማዕድን ዘርፉ 453 ሚልዮን ዶላር እና አምራች ኢንደስትሪው በ378.5 ሚልዮን ዶላር ገቢ የተገኘባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡
የዘጠኝ ወራቱ ውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ከእቅዳችን አንጻር በመጠኑ ዝቅ ያለ ቢሆንም ሀገራችን ላይ ካጋጠሙ ችግሮች አንጻር እና ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ጭማሬ የታየበት መሆኑ አይካድም፡፡
ምንም እንኳን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ፍላጎት ቢኖርም በበጀት ዓመቱ የሚጠበቅብንን የውጭ ዕዳ ክፍያ በአግባቡ ለመክፈል ችለናል።
በየጊዜው እያደገ የመጣውን የሥራ አጥነት ለመቀነስ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተነድፈው ሲሰራባቸው የቆዩ ሲሆን፣ ባለፉት 9 ወራት ውስጥ 1.4 ሚልዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ የተፈጠረው የሥራ ዕድል ሰፊውን ቁጥር ቢሸፍንም፣ ሞያዊ ሥልጠና ወስደው በውጭ ሀገራት ማለትም በኳታር፣ በዮርዳኖስና በተባበሩት የዓረብ ኤምሬቶች የሥራ እድል የተመቻቸላቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
አሁንም በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፈተና እየገጠመን ያለው ከዋጋ ግሽበት ጋር በተገናኘ ሲሆን፥ ከአምናው የሚያዚያ ወር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ግሽበቱ 36.6% ደርሷል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሐዝ ለማውረድ በርካታ ርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት ጥረታችን በቂ ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል፡፡
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ያጋጠሙ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የጥሬ ዕቃዎች መናር፣ በሀገራችን ያጋጠሙ ግጭቶች እና በቅርብ ወራት ደግሞ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የፈጠረው ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት የሀገራችንን የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሻቅብ ምክንያት ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በመንግሥት በኩል አሁንም የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት የተለያዩ ርምጃዎችን ከመውሰድ አልተቆጠበም።
የስንዴ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በርካታ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል። ተጨባጭ ተግባራትና አስተዳደራዊ ርምጃዎችም እየተወሰዱ ናቸው።
ያልተመጣጠነውን የመንግሥት ገቢና የወጪ ለማስተካከል በቀጣይ የመንግስት ወጪን ከሀገር ውስጥ ገቢ በተገቢው መልኩ ለመሸፈን፣ የታክስ ሥርዓቱን ማዘመን እና በሂደት ላይ ያሉትን እንደ ንብረት ታክስ፣ የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻዎያችን በአፋጣኝ ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል።
የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ሕጉን ለማሻሻልም እየተሠራ ይገኛል። ከወጪ አንፃር መከናወን የሌለባቸውን ፕሮጀክቶች ሀብት ሳይባክን ወደ ቀጣይ ሂደት እንዳያልፉ በማድረግና ፕሮጀክቶችን ቅደም ተከተል በማስያዝ፣ መሸጋገር የሚችሉትን ወደሚቀጥለው ጊዜ በማሸጋገር ወጪን ለመቀነስ ጥረት ተደርጓል።
በቀጣይ ጊዜያት በኢኮኖሚያችን ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቀነስ የተለያዩ አንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።
መሠረታዊነታቸው የታመነባቸው እንደ ስንዴ፣ ዘይት፣ የሕጻናት ምግብ እና ስኳር የመሳሰሉ የፍጆታ ዕቃዎች አስመጪዎች በፍራንኮ ቫሉታ አሠራር የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ በመጠቀም እንዲያስገቡ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል።
የመድኃኒት፣ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ ዘይት፣ እና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች ግዥን በተገቢው ሁኔታ እንዲካሄድ፣ በእነዚህ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ መንዛዛት እንዳይኖር በግዥ ሥርዓቱ ላይ አስፈላጊው ማስተካከያ ይወሰዳል።
ከዚህ በተጫማሪ ከአንዳንድ አስመጭዎች ጋር በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል በተደረገ ውል አሁን ላይ መክፍል ሳያስፈልግ በ“deferred letter of credit” አማካይነት እንደ ዘይት፣ ስንዴ እና ስኳር ያሉ መሠረታዊ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡቡት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል።
ነዳጅን በተመለከተ የዋጋ ንረቱን ተከትሎ የሚኖርውን የበጀት ጫና መቀነስ ይቻል ዘንድ፣ ወጥ ከሆነው የመንግሥት የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ በመውጣት በተጠና መንገድ ድጎማው ለሚያስፈልጋቸው አካላት ብቻ እንዲሆን በዕቅድ እየተሠራ ነው።
በበጋ ስንዴ ምርት ላይ የታየውን አበረታች ውጤት በማጎልበት፣ የስንዴ ምርትን መሉ በመሉ ከውጪ ማስገባት ለማስቀረት የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የምርቱ መጨመር በራሱ ገበያውን ለማረጋጋት ጉልህ ሚና አንደሚኖረው ይጠበቃል።
ይህ ክሥተት የራሳችንን ውስጣዊ ዐቅም በደንብ እንድንፈትሽ ዕድል በመፍጠሩ ክሥተቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በዘላቂነት በመሠረታዊ ሸቀጦች ራስን ለመቻል በምንወስዳቸው ርምጃዎች እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ጥረታችን ኢኮኖሚው ተግዳሮቶችን ከመቋቋም አልፎ ተግዳሮቶችን ወደማሸነፍ የሚያሸጋግር መሆን አለበት። መንግሥት፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ፣ ምሁራንና ሕዝቡ፣ ሁሉም የየድርሻቸውን መወጣት ከቻለ በእርግጥም ጥረታችን ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም።
በእስካሁኑ ጉዞአችን የገጠሙን ፈተናዎች ጥንካሬአችንን የተገዳደሩ ቢሆኑም በቀላሉ ስላልወደቅን አጠንክረውን አልፈዋል፡፡
ፈተናዎቻችንን በጽናት ተቋቁመን ባለፍን ቁጥር አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ማለታችን አይቀርም፤ የምናስመዘግባቸው ድሎች በሚፈጥሩልን ወኔ ተበረታትተን አሻግረን የብልጽግና ተስፋችንን እንደምናይ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ተስፋችን ተሳክቶ ለትውልዱ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማውረስ እንድንችል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት
ግንቦት 2፣ 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.