በኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልልታ የተመራ ልዑክ በድሬዳዋ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኘ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልልታ የተመራ ልዑክ በድሬዳዋ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የልማት እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።
የስራ ጉብኝቱ በተለያዩ ችግሮች ወደ ስራ ያልገቡ ፋብሪካዎች አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ስራ ገብተው ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የአገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል።
ለአብነት ልዑካኑ ለ6 ወራት በብድር እና በካፒታል ዕጥረት ተቋርጦ የነበረው እና ችግሩ ተፈትቶለት ወደ ስራ የተመለሰውን የድሬዳዋ ጄ ኤፍ ጂ የፕላስቲክ ከረጢት ፋብሪካ ተመልክተዋል።
በተጨማሪም በ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ካፒታል በኢንዱስትሪ መንደር የተገነባውን የመኪናና የባለሶስት እግር ታክሲ መገጣጠሚያ የሬድዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪን የስራ እንቅስቃሴዎች ጎብኝተዋል።
ሚኒስትር ደኤታው አቶ ታረቀኝ÷ በአሁን ወቅት በከተማዋ በተለያዩ ችግሮች ስራ ያቋረጡ ኢንዱስትሪዎች ስራ በሚጀመሩበት መሠረታዊ መፍትሄዎች እና አቅጣጫዎች ላይ ከሚመለከታቸው የአስተዳደሩ እና የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ኢንዱስትሪዎቹ ያጋጠሟቸው ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተጠቁሟል።