በአቶ ዑመር ሁሴን የተመራ ልዑክ በደሴ ዙሪያ ወረዳ የጠባሲት ንዑስ ተፋሰስን ጎበኘ
በጉብኝቱ ላይ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴንን ጨምሮ በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ፣ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለ ማርያም ከፍያለው፣ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴንና ሌሎች የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች መገኘታቸውን ከደቡብ ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በግብርና ሚንስቴር አቶ ዑመር ሁሴን የተመራ የልዑካን ቡድን በትናንትናው ዕለት በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በክላስተር የለሙ የማንጎ እርሻዎችና የቆላ ፍራፍሬ ችግኝ ጣቢያን ጎብኝቷል።
በ500 ሄክታር መሬት ላይ የማንጎ ክላስተር በመፍጠር አርሶ አደሮችን ወደ ፍራፍሬ ልማት ማስገባት እንደተቻለም ነው የተገለጸው።
5 ሺህ 189 አርሶ አደሮች በወረዳው ማንጎ ክላስተር በመታቀፍ ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል።
በወረዳው የፍራፍሬ ችግኝ የሚያዘጋጁ 6 ማህበራት ያሉ ሲሆን፥ የቆላ ፍራፍሬዎችን ለአጎራባች ወረዳዎችና ለአፋር ክልል ያቀርባሉ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው፥ ችግኞችን በበቂ ሁኔታ በማዘጋጀት በክላስተር በማደራጀትና ስልጠና በመስጠት አርሶ አደሩን ፍራፍሬ አምራች እንዲሆን እየሰራን ነው ብለዋል ።