Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን ውጥረት እያባባሰችው ነው ሲሉ ቻይና እና ሩሲያ ወቀሱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና እና ሩሲያ ፒዮንግያንግ የምታደርገውን የሚሳኤል ሙከራ መቀጠሏን ተከትሎ አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ያለውን ውጥረት እያባባሰች ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ወር የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ በአሜሪካ ቀርቦ በተመድ ሊጣልባት የነበረውን ማዕቀብ ሁለቱ ሃገራት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ሃገራቱ በሰሜን ኮሪያ ላይ ሊጣሉ የታቀዱ ተጨማሪ ማዕቀቦችን በመቃወም እንዲሁም በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለውን ውጥረት ለማርገብ ብቸኛው አማራጭ ውይይት እንደሆነም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ቤጂንግ እና ሞስኮ ትናንት በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ዋሺንግተን በቀጠናው ውጥረት ቀስቅሳለች ሲሉ አውግዘዋል፡፡

ጉባዔው ቻይና እና ሩሲያ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ወር በአሜሪካ በቀረበውና በሰሜን ኮሪያ ላይ እንዲጣል የታቀደውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ የተቃወሙበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ለመጠየቅ ያለመ ነው።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና አምባሳደር ዣንግ ጁን በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንዲቀንስ ጠይቀዋል፡፡

“አሜሪካ ማድረግ የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ” ያሉት አምባሳደሩ ፥ ለአብነትም ሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በተወሰኑ አካባቢዎች ማቃለልና ዋሺንግተን ከደቡብ ኮሪያ ጋር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓን ማቆም አለባትም ነው” ያሉት፡፡

አምባሳደሩ አክለውም ምንም ቅድመ ሁኔታ ሳይኖር ለውይይት ዝግጁ ስለመሆን ማውራት ብቻ ሳይሆን ወደ እርምጃ መግባት ቁልፉ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩሲያ ምክትል አምባሳደር አና ኢቭስቲግኔቫ በበኩላቸው፥ በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ጠይቀዋል።

ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋትና ምዕራባውያን ለተፈጠሩ ውጥረቶች እሷኑ መውቀሳቸውን ማቆም አለባቸውም ነው ያሉት፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ በኒውክሌር እና ባለስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራሞቿ ላይ ተመድ የጣለባትን ማዕቀብ ችላ በማለት በዚህ ዓመት ከ12 በላይ አህጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤልን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያ ሙከራዎችን አድርጋለች።
ከ2017 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስምንት የአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል በምስራቃዊ የባህር ዳርቻዋ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሞክራለች።

የተባበሩት መንግስታት የጣለው ማዕቀብ ሰሜን ኮሪያ በጣም የሚያስፈልጋት ሰብዓዊ እርዳታ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም ቢልም፥ የእርዳታ ድርጅቶች በንግድና የባንክ እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣሉ ክልከላዎች በሚያደርጉት አቅርቦት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸዋል።

በተመድ የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ጄፍሪ ዴላውረንቲስ ከፒዮንግያንግ ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ውይይት እንፈልጋለን ማለታቸውን አር ቲ እና ፕረስ ቲቪ ዘግበዋል።

በተጨማሪም ቻይና እና ሩሲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ተጨማሪ ማዕቀብ በመቃወም “ገደብ የለሽ” ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ከዓለም አቀፍ ደህንነት በላይ ከፍ አድርገው ይሆን ወይ ሲሉም ጠይቀዋል።

ቤጂንግ እና ሞስኮ በየካቲት ወር ላይ “ገደብ የለሽ” አጋርነት ብለው ያወጁትንም ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.