Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪነትንና ጽንፈኝነትን ለመዋጋት ከቀደመው ጊዜ በበለጠ በጋራ እንደሚሰሩ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪነትንና ጽንፈኝነትን ለመዋጋት ከቀደመው ጊዜ በበለጠ በጋራ እንደሚሰሩ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አስታወቁ፡፡
የሁለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በኦሮሚያ ክልል አሸባሪው ሸኔ በፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት እና በቀጣይ የሽብር ጥቃቶችን መመከት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ክልሎቹ የሽብር ቡድኑ ለፈጸመው አረመኔያዊ ተግባር የእጁን እንዲያገኝ አስቀድሞ ከተጀመረው ዘመቻ ባለፈ በጋራ ሕግ የማስከበር ሥራውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ ጠላቶቻችን ብሔርን ለይተው በማጥቃት እርስ በርሳችን እንድንጫረስ የሚያደርጉት የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ነው ያሉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፥ አመራሩ ይህን በግልጽ ተገንዝቦ አቋም ሊይዝ ይገባል ብለዋል።
ከሕዝባችን ጋር በመቀናጀት በቀጣይ ተመሳሳይ የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት በጋራ ተባብረን መስራታችንን ማረጋገጥ አለብንም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።
ወደፊት የሚመጣ ችግር ካለ በጋራ ለመከላከል በየደረጃው ያለውን አመራር እያጣራን በመረጃ ላይ የተመሰረተ እርምጃ በመውሰድ የሕዝባችንን ሰላም እና ደህንነት እናረጋግጣለንም ብለዋል።
የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች መረጃ እየተቀያየሩ እና የጋራ ኮሚቴ እያዋቀሩ የጋራ ጠላታቸውን በጋራ እንደሚዋጉም አስታውቀዋል።
ሸኔ የአማራ ጠላት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ መላ ኢትዮጵያውያን ሕግ የማስከበር እርምጃውን በጽናት መደገፍ አለባቸውም ነው ያሉት፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ ጠላት ከለውጡ ጀምሮ በክልሉ ግጭቶችን በማስነሳት፣ ግድያዎችን በመፈጸም እና ጥቃቶችን በማድረስ መቀጠሉን አንስተዋል።
በዚህም ሕዝቡ፣ አመራሩ እና የጸጥታ ኃይሉ ተፈትኗል መስዋዕትነትም ከፍሏል ነው ያሉት፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ሸኔ በተደጋጋሚ በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚፈጽመው የአማራ እና የኦሮሞን ሕዝብ ለማለያየት መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ ላይ ፍርሀት ለማስፈን ዓልሞ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የሸኔ የሰሞኑ ተግባር የእያንዳንዳችንን ልብ ቢሰብርም የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት ግን በፍጹም ሊሰብር አይችልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ፥ ሁለቱ ክልሎች በተሻለ በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የሽብር ቡድኑን እኩይ ድርጊት አመራሩ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን፥ አሸባሪው የእጁን እንዲያገኝ ያለምህረት እርምጃ በመውሰድ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል ተያይዞ መስራት ይጠበቅበታልም ብለዋል።
ሁለቱም ክልሎች በጋራ ምን መስራት እንደሚችሉ የሚያውቁ እና በተግባር ያረጋግጡ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ አሁንም ይህንኑ መንገድ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የሁለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በውይይታቸው በአጎራባች አካባቢ የተቀናጀ ሥራ በመስራት ጽንፈኝነትን እንታገላለን የሽብር ጥቃቶችንም እንመክታለን ብለዋል።
በሸኔ እና በሌሎች ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የተጀመረውን እርምጃ በወታደራዊም በፖለቲካዊም ሥራችን ማጠናከር አለብንም ነው ያሉት።
በአልአዛር ታደለ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.