Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት በሰላም  ለመፍታት መወሰኗ የቀጣናው ሰላም ተምሳሌትነቷን ዳግም የሚያረጋግጥ ነው – አምባሳደር አለልኝ አድማሱ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኗ የቀጣናውና የዓለም ሰላም ተምሳሌትነቷን ዳግም የሚያረጋግጥ መሆኑን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ገለጹ።

እስራኤል በኢትዮጵያ ግጭቶችን በሰላም አማራጭ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምትደግፍም ነው አምባሳደሩ ያረጋገጡት፡፡

መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በሀገር ሽማግሌዎች በመላክ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም ቢሆን የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ቁርጠኝነቱን በተግባር ማሳየቱም እንዲሁ፡፡

አሁን ላይም መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አለመግባባትና ግጭቶችን በዘላቂነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፥ ሀገራቸው እስራኤል የሰላምንና የትብብርን አስፈላጊነት በአግባቡ ትገነዘባለች፤ ከዚህ አኳያ በዙሪያዋ ካሉ የዓረቡ ዓለም አገራት ጋር በቅርበት እየሰራች ነው ብለዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት አምባሳደሩ፥ ለመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ቅርብ የሆነችው ኢትዮጵያ ችግሮችን በሰላም አማራጭ ለመፍታት እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

መንግሥት የጀመረው የሰላም አማራጭ ሂደት ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የሚጠቅም መሆኑን አንስተው፥ የሰላም አማራጩ ለጎረቤት ሀገራት፣ ለአፍሪካና ለቀጣናውም አስተማሪ ነው ብለዋል።

እስራኤል የኢትዮጵያን የሰላም አማራጭ መንገድ እንደምትደግፍ ያነሱት አምባሳደሩ፥ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን መንግሥት ፊቱን ወደ ልማት ሙሉ ለሙሉ ለማዞር ያስችለዋል ነው ያሉት።

ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ ሰላም ሲሰፍን የዓለም ሀገራት  ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የልማትና ሌሎችም ትብብሮች እንደሚያጠናክሩም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ አፍሪካን አንድ ያደረገችና በሰላም አብረን እንኑር የምትል የሰላም ምልክት ናት” ያሉት  አምባሳደር አለልኝ፥ በዓለም ሰላምነ በማስከበር ረገድ  ያላትንም ሚና አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኗ የቀጣናውና የዓለም ሰላም ተምሳሌትነቷን ዳግም የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.