ሌብነት ነፃነትን የሚገፍ እና ውርደት መሆኑን በመረዳት ዜጎች እያሳዩት ላለው ፍቅር በቅንነት ማገልገል ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አመራሩ ሌብነት ነፃነትን የሚገፍ እና ውርደት መሆኑን በመረዳት ዜጎች እያሳዩት ላለው ፍቅር በቅንነት ማገልገል ይገባዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከከተማ እስከ ወረዳ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች የ2014 ዓ.ም አፈፃፀም ግምገማና የ2015 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫ በተመለከተ ላለፉት አራት ቀናት ሲያካሂድ የቆየው ግምገማዊ የውይይት መድረክ ተጠናቋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማጠቃለያ መድረኩ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት የዕቅድ ግብአቶች ከታች እንዲመጡ ከማድረግ ጀምሮ ህዝባችን በምርጫው የሰጠንን ይሁንታ በመጠበቅ የብልፅግና ፓርቲን ሰው ተኮር ዓላማዎች ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት ተደርጓል።
በሰላም፣ በሜጋ ፕሮጀክት አፈፃፀም፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎችም ተቋማት የተጀማመሩ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ከንቲባዋ አስረድተዋል።
አልፎ አልፎ ብቅ ብቅ የሚሉ የጽንፈኝነት አመለካከቶች የጥቂት ጽንፈኞች እንጂ የህዝብ ፍላጎቶች አለመሆናቸውን የገለፁት ከንቲባዋ አንድ እግርን ከብልፅግና አንድ እግርን ከጽንፈኛ አድርጎ መጓዝ እንደማይቻል አስገንዝበዋል።
ሌብነት ነፃነትን የሚገፍ እና ውርደት መሆኑን በመረዳት አገር ሲለወጥ እለወጣለሁ በማለት ህዝባችን እየሰጠን ላለው ፍቅር በቅንነት መስራት እንደሚገባም ከንቲባ አዳነች አሳስበዋል።