Fana: At a Speed of Life!

የአየር ክልላችንን ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅ የሚያስችል ቁመና ላይ ነን- ሌ/ጀ ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአየር ክልሉን ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅና መከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ እንደገለጹት÷አየር ኃይሉ ቴክኖሎጂ በማፍለቅና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ቀዳሚ የአየር ኃይል የመሆን ራዕይ ሰንቋል፡፡

የአየር ኃይል አባላት ቀደም ባሉት ዓመታት በፖለቲካ አመለካከት እና በብሔር ማንነት ተከፍለው አየር ኃይሉ ችግር ውስጥ ወድቆ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ ይሄንን አስተሳሰብ በመቀየር የሰራዊት አባል ሁሉ ከፖለቲካና ከብሔር አስተሳሰብ እንዲወጣ በማድረግ ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው አየር ኃይል መገንባት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የኢፌዴሪ አየር ኃይል “ለታላቅ አገር ታላቅ የአየር ኃይል” በሚል መሪ ሀሳብ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚረዳ የሰው ኃብት፣ ዘመናዊ ትጥቆችና የውጊያ መሰረተ ልማት አሟልቷልም ነው ያሉት፡፡

ሰራዊቱ የኢትዮጵያን የአየር ክልል 24 ሰዓት ሙሉ በተጠንቀቅ እየጠበቀ መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጀነራል ይልማ÷ አየር ኃይሉ በማንኛውም ሁኔታ ለግዳጅ ዝግጁ የሆነ ኃይል ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ሰራዊቱ በየቀኑ የመሳሪያ፣ የአካልና የእውቀት ፍተሻ በማድረግ የተሟላ ስነ-ልቦና ተላብሶ አገሩን እየጠበቀ እንደሆነ  መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.