Fana: At a Speed of Life!

ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት የፀደቀው ምክረ ሃሳብ መንግስት ለሰላማዊ አማራጭ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ነው – ቢልለኔ ስዩም

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ያፀደቀው የሰላም ምክረ ሃሳብ የመንግስትን ለሰላማዊ አማራጭ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለፁ።
 
ኃላፊዋ ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
 
በመግለጫቸው በሰላም እና ጸጥታ፣ ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ባሉ ጥረቶች፣ በሰብዓዊ ድጋፎች እና አረንጓዴ አሻራ ላይ አተኩረዋል።
 
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ በመስጠቱ ዙሪያ፥ በመጪዎቹ ሳምንታት የተኩስ አቁም እንዲደረስ፣ የሰላም ውይይት እንዲሁም ሌሎች በእንጥልጥል የቀሩ ጉዳዮች ደግሞ በብሄራዊ ምክክሩ እንዲዳሰሱ ለማድረግ የሚያስችል የሰላም ረቂቅ ሰነድ ይፋ መደረጉን አንስተዋል፡፡
 
በሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ የተዘጋጀው ሰነዱ መንግስት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ በሚፈታበት ሁኔታ ላይ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አመላካች ነውም ብለዋል፡፡
 
የሰላም ውይይት ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ የሚያስፈልገው አይደለም ያሉት ቢልለኔ፥ የትግራይ ህዝብ የህወሃት እስረኛ ሆኖ ሊቀጥል አይግባም ነው ያሉት፡፡
 
ህወሃት ፍላጎቱን ለማስፈፀም በትግራይ ክልል በተከታታይ የሀይል አማራጮችን እየተጠቀመ እንደሚገኝ ያነሱት ኃላፊዋ፥ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም ጭፍጨፋዎችን እንደሚፈፅም አመልክተዋል፡፡
 
በህገወጥ መንገድ የሰበሰበውን የውጭ ምንዛሪ፣ ለመጠባበቂያነት የተቀመጡ የነዳጅ፣ የምግብና የመሳሰሉ ግብአቶችን ለዚሁ እኩይ ተልዕኮው እንደሚጠቀም ጠቁመዋል።
 
ቡድኑ ይህን ሁሉ እኩይ ተግባራት እየፈፀመ ባለበት ሁኔታ መንግስት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ነገሮችን በሆደ ሲፊነት ሲመለከት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
 
መንግስት ከጦርነቱም በፊትም ሆነ በጦርነቱ ወቅት እንዲሁም ከጦርነቱም በኃላ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርግ እንደቆየና በህወሃት በኩል ለሰላም አማራጭ የተሰጠ ሥፍራ አለመኖሩን በማንሳት አሁንም በዚሁ ባህሪው መቀጠሉን ነው ያነሱት።
 
ህወሃት የሀሰት ክሶችን በማንሳትና የተሳሳቱ ትርክቶችን በመንዛት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በተሳሳተ አቅጣጫ ለመምራት ሙከራ እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
 
በመሆኑም በትግራይ ክልል ዙሪያ ብዥታ ሊኖር እንደማይገባና በክልሉ መላሶ ግንባታና መሰረታዊ ድጋፎች ላይ መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
 
መንግስት ባለሙያ በመላክም ሆነ እዛው ያሉውን የሰው ሀያል በመጠቀም በክልሉ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎት ለመመለስ ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም ደግሞ አንዳንድ በመሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ እንደሚፈልግም ገልፀዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት መሪነትበማንኛውም ጊዜ እና ቦታ የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
 
ኃላፊዋ ከሰሞኑ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ ተጓዦች ላይ እየተደረገ ስለሚገኘው ቁጥጥር አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
 
በምላሻቸውም ህወሃት በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ወረራ በፈፀመበት ወቅት የዘረፋቸውን የመንግስት ማህተሞች በመጠቀም ሀሰተኛ መታወቂያ በማሳተም ለእኩይ ተግባሩ እያዋለ በመሆኑ፥ ይህንን ድርጊቱን ለመግታት እና ተከታትሎ ለመያዝ በተወሰደ እርምጃ የተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.