በቀጣዮቹ 10 ቀናት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ ይቀጥላል- ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ዝናቡ ቀጣይነት እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ደቡባዊ የሀገሪቱ አካባቢዎችም ሁለተኛውን የዝናብ ወቅታቸውን ቀስ በቀስ ያገኛሉ የተባለ ሲሆን፥ በአንጻሩ በሰሜንና በሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ መጠኑ ይቀንሳል ተብሏል፡፡
የክረምቱ ዝናብ በአብዛኛው ወደ ምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚያመዝን ሲሆን÷ የዘንድሮው የክረምት ዝናብ በአንዳንድ የሰሜንና የሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በአወጣጥ ረገድ ለተወሰኑ ቀናት የመዘግየት አዝማሚያ ሊኖረው እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጅ ኢንስቲትዩት መረጃ አመላክቷል፡፡
በሚቀጥሉት 10 ቀናት ሁሉም የወለጋና የሸዋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ቡኖ በደሌ፣ አርሲ፣ አዲስ አበባ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ጎንደር፣ ባህር ዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን፣ ሰሜን ሸዋ እንዲሁም ከትግራይ ክልል የምዕራብና የሰሜን ምዕራብ ዞኖች፣ የቤኒሻንጉል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ እና ጌዲዮ በስተቀር መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡
እንዲሁም የሲዳማ እና የጋምቤላ ዞኖች፣ ደቡብ ጎንደር፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የዋግኽምራ፣ የደቡብ፣ የመካከለኛውና የምሥራቅ ትግራይ ዞኖች፣ የአፋር ዞን 3 እና 5፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ጉጂ፣ ድሬዳዋና ሐረሪ ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የሰገን ሕዝቦች፣ የምዕራብ ኦሞ እንዲሁም የፋፈንና የሲቲ ዞኖች በአንዳንድ ሥፍራዎቻቸው ላይ በአብዛኛው ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
የተቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛው ደረቅ ሆነው እንደሚሰነብቱ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
በሌላ በኩል በቀጣዮቹ 10 ቀናት በአብዛኛው በመካከለኛው፣ በደቡብና በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙት ተፋሰሶች ላይ የተሻለ እርጥበት ሊኖራቸው እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ በአብዛኛው ዓባይ፣ የላይኛውና የመካከለኛው ባሮአኮቦ፣ ኦሞጊቤ፣ ስምጥሸለቆ፣ የላይኛው አዋሽ፣ ተከዜ፣ ዋቢሸበሌ እንዲሁም የገናሌዳዋ ተፋሰሶች ላይ ከከፍተኛ እርጥበት እስከ እርጥበታማ የእርጥበት መጠን እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
ከሚኖረው ከፍተኛ እርጥበት በተጠቀሱት ተፋሰሶች ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎቻቸው ላይ ጥንቃቄና ክትትል ያስፈልጋል ብሏል፡፡